መስከረም 07 ቀን 2019ዓ.ም.(መናኸሪያ ሬዲዮ) የአሜሪካ ኤምባሲ ዶሎ ዞንን በተመለከተ ያወጣው የጉዞ ማስጠንቀቂያ በአካባቢው ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ አያንጸባርቅም! የሶማሌ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ፣ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ሴፕቴምበር 16/2026 ዶሎ ዞንን በተመለከተ ያወጣውን የጉዞ ማስጠንቀቂያ ተመልክቷል። በዚህም መሰረት የወጣው ማስጠንቀቂያ በችኮላ የወጣና በዶሎ ዞን ያለውን ተጨባጭ የሰላምና የደኅንነት ሁኔታ በትክክል የማያንጸባርቅ ፤ በአካባቢው ያለውን ሁኔታ በየጊዜው ከሚከታተሉት የክልሉ አስተዳደር የደህንነትና ፀጥታ ተቋማት ጋር በቂ የመረጃ ማጣራትና ምክክር ሳይደረግበት የወጣ ነው። የክልሉ አስተዳደርና የፀጥታ ተቋማት ባረጋገጡት መሠረት፣ ዞኑ ሰላማዊና የተረጋጋ ነው። የመንግሥት ተቋማትም መደበኛ ኃላፊነታቸውን በሙሉ እየተወጡ ሲሆን፣ የሰው፣ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ፣ የንግድ ሥራዎች፣ የማኅበራዊ አገልግሎቶችና ሌሎች ዕለታዊ ተግባራት በመደበኛነት እየተከናወኑ ይገኛሉ። የሶማሌ ክልል መንግሥት ለነዋሪዎች፣ ለእንግዶችና በክልሉ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ደኅንነት ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል። ልዩ ጥንቃቄ የሚያስፈልግ የፀጥታ ሁኔታ ካጋጠመም፣ የሚመለከታቸው ተቋማት ትክክለኛ፣ ወቅታዊና ይፋዊ መረጃ ለሕዝቡ ያደርሳሉ። በመሆኑም፣ የዲፕሎማሲ ተቋማትና የጉዞ ማስጠንቀቂያዎችን የሚያወጡ ሌሎች አካላት መረጃዎችን ከማሰራጨታቸው በፊት መሬት ላይ ያሉ እውነታዎችን በአግባቡ እንዲያጣሩና ከሶማሌ ክልል የሚመለከታቸው ተቋማት ጋር እንዲመካከሩ እንጠይቃለን። በተሟላ መረጃ ላይ ያልተመሠረተ ማስጠንቀቂያ አላስፈላጊ ሥጋት ከመፍጠሩም በላይ፣ በክልሉ ስላለው ሰላምና መረጋጋት የተሳሳተ ገጽታ ሊፈጥር እንደሚችልም ማስገንዘብ እንወዳለን። የሶማሌ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ፣ የዶሎ ዞን ሰላማዊና የተረጋጋ መሆኑን፣ የዞኑ አስተዳደር የደህንነት እና የፀጥታ ተቋማትም አጠቃላይ ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተሉ መሆኑን በድጋሚ ያረጋግጣል።
የሶማሌ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ መስከረም 7/2019 ጅግጅጋ
___
ሀሳብ እና‘ሳ‘ፍራለን
ምላሽ ይስጡ