ሚያዚያ 12 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የአሜሪካዋ ቴነሲ ግዛት ከመዋለ ሕፃናት እስከ 12ኛ ክፍል ባሉ ሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የጦር መሣሪያ ደህንነት ትምህርት የግዴታ እንዲሆን የሚደነግገውን ሕግ ተግባራዊ ልታደርግ ነው።
በ2024 የጸደቀው ይህ ሕግ በ2025-2026 የትምህርት ዘመን በይፋ ሥራ ላይ እየዋለ ሲሆን፣ ይህም ቴነሲን እንዲህ ያለውን ትምህርት በግዴታነት የደነገገች የመጀመሪያዋ የአሜሪካ ግዛት ያደርጋታል።
የትምህርት መርሃ ግብሩ ተማሪዎች እውነተኛ የጦር መሣሪያዎችን ከአሻንጉሊት እንዲለዩ፣ መሣሪያዎች በቤት ውስጥ እንዴት በጥንቃቄ መቀመጥ እንዳለባቸው እንዲረዱ እና በአጋጣሚ የጦር መሣሪያ ሲያጋጥማቸው ምን ዓይነት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው የሚያስተምር ነው።
ይህ ሥልጠና ምንም ዓይነት ጥይት ወይም የተኩስ ልምምድን የማይጨምር ሲሆን፣ ትኩረቱ ሙሉ በሙሉ በደህንነት ግንዛቤ ላይ ብቻ የተገደበ ነው።
ትምህርት ቤቶች ይህንን ሥልጠና ለተማሪዎች በሚሰጡበት ወቅት ከሕግ አስከባሪ አካላት ጋር በጋራ የመሥራት ዕድል ተሰጥቷቸዋል። ይህም ተማሪዎች ስለ ጦር መሣሪያዎች ያላቸውን ግንዛቤ በማሳደግ በአጋጣሚ የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመቀነስ የታለመ ስትራቴጂ መሆኑ ተገልጿል።
“ዋናው ግባችን ተማሪዎች የጦር መሣሪያ ሲያዩ መሣሪያውን ሳይነኩ ራሳቸውን እንዲከላከሉና በአፋጣኝ ለአዋቂዎች እንዲያሳውቁ ማስተማር ነው።” ተብሏል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ