መስከረም 08 ቀን 2019ዓ.ም.(መናኸሪያ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እየጨመረ የመጣውን የሃይል ፍላጎት ለመመለስና አዳዲስ ደንበኞችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ተቋሙ አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ባከናወነው ሥራ ለረዥም ዓመታት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሳያገኙ የቆዩ ከ5ሺህ በላይ አዳዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል፡፡ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ የሆኑት በኦሮሚያ ክልል በአምስት ዞኖች የሚገኙ ምስራቅ ጉጂ፣ጉጂ፣ ምዕራብ አርሲ፣ ቦረና እና ምስራቅ ቦረና ዞኖች የሚገኙ ደንበኞች ናቸው፡፡ ከነዚህ መካከል በጉጂ ዞን ኦዶ ሻኪሶ ወረዳ እንዲሁም በቦረና ዞን ተልተሌ ወረዳ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ይገኙበታል። በተጨማሪም በአካባቢዎቹ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ተቋማት፣ ፖሊስ ጣቢያዎች እና የማዘጋጃ ቤት ቢሮዎችን ጨምሮ በርካታ ማህበራዊና የመንግስት ተቋማት የኤሌክትሪክ ሃይል ማግኘት ችለዋል። ቀደም ሲል በአካባቢዎቹ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ባለመኖሩ ነዋሪዎች በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎቻቸው ላይ ከፍተኛ ጫና እና እንግልት ይደርስባቸው ነበር። አሁን ላይ ተቋሙ ባከናወነው አቅምን መሰረት ያደረገ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ህብረተሰቡ ከነበረበት እንግልት ወጥቶ ጥራት ያለው ማህበራዊ አገልግሎት እንዲያገኝ እና የዕለት ተዕለት ኑሮው እንዲቃለል መልካም እድል ፈጥሯል። ከዚህ በተጨማሪ ተቋሙ ከዋናው ግሪድ ርቀው የሚገኙ የገጠር ከተሞችንና ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚስችሉ የሶላር ሚኒ ግሪድ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ ወደ ስራ ገብቷል፡፡ ተቋሙ እ.ኤ.አ በ2030 ከዋናው ግሪድ 65 በመቶ እንዲሁም በአማራጭ የኃይል ምንጮች 35 በመቶ የሚሆነውን ህብረተሰብ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ርብርብ እያደረገ ይገኛል፡፡
___
ሀሳብ እና‘ሳ‘ፍራለን
ምላሽ ይስጡ