መስከረም 05 ቀን 2019ዓ.ም.(መናኸሪያ ሬዲዮ) የባርሴሎናው ወጣት አጥቂ ላሚን ያማል የ2026 የባሎንዶር ክብር ለእሱ እንደሚገባው በራስ መተማመን የተሞላበት አስተያየት የሰጠ ሲሆን፣ ራሱን እና ፈረንሳያዊውን አጥቂ ኪሊያን ምባፔን አሁን ላይ በዓለም እግር ኳስ ውስጥ ያሉ ሁለት ምርጥ ተጫዋቾች እንደሆኑ ተናግሯል። የ19 ዓመቱ የፊት መስመር ተጫዋች በውድድር ዘመኑ በባርሴሎና እና በስፔን ብሔራዊ ቡድን ውስጥ አስደናቂ የስኬት ጊዜን ያሳለፈ ሲሆን፣ በተለይም ስፔን የዓለም ዋንጫን እንድታነሳ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በክለብ ደረጃም ከባርሴሎና ጋር በርካታ ዋንጫዎችን በማሳካት እና ድንቅ የግል ብቃት በማሳየት፣ በሁሉም ውድድሮች በ45 ጨዋታዎች ተሰልፎ 24 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን 17 ግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል። በላሊጋው በ28 ጨዋታዎች ተሰልፎ 16 ግቦችን በማስቆጠር በከፍተኛ ግብ አግቢነት 4ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀ ሲሆን፣ 11 ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል ደግሞ የሊጉ ከፍተኛ ኳስ አመቻች ሆኖ አጠናቋል። በያዝነው የ2026/27 አዲስ ውድድር ዘመንም በ4 ጨዋታዎች 4 ግቦችን በማስቆጠር አስደናቂ ብቃቱን እንደቀጠለ ይገኛል። ከባርሴሎና ጋር የላሊጋ ሻምፒዮንነትን የተቀናጀ ሲሆን፣ ከስፔን ብሔራዊ ቡድን ጋር ደግሞ የ2026 የዓለም ዋንጫን በማንሳት የታሪክ አካል ሆኗል። ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ያስመዘገባቸው እነዚህ አስደናቂ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የስታቲስቲክስ የበላይነቶች ለዓለማችን ከፍተኛ የግል ክብር (Ballon d’Or) ቀዳሚ ተወዳዳሪ እንደሚያደርጉት የሚታመን ሲሆን፣ ተጫዋቹ ራሱም ይህ የግል ክብር እንደሚገባው በአጽንኦት ተናግሯል። የዘንድሮው የባሎንዶር አሸናፊ ማን እንደሆነ በቀጣዩ ወር የሚታወቅ ይሆናል።
___
ሀሳብ እና‘ሳ‘ፍራለን
ምላሽ ይስጡ