ነሐሴ 23 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) ማንቸስተር ሲቲዎች የዝውውር መስኮቱ ከመዘጋቱ በፊት የኤቨርተኑን ኢሊማን ንዲያዬን ለማስፈረም ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ጋዜጠኛ ቤን ጃኮፕስ ዘግቧል። ማንቸስተር ሲቲ የማጥቃት መስመሩን ለማጠናከር በሚያደርገው የዝውውር እንቅስቃሴ የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን አጥቂ የሆነውን ንዲያዬን ለማስፈረም ፍላጎት ማሳየቱን ተከትሎ፣ ኤቨርተኖች ለተጫዋቹ 70 ሚሊዮን ፓውንድ የዝውውር ዋጋ መጠየቃቸው ተሰምቷል። የ26 ዓመቱ ሴኔጋላዊ የክንፍ መስመር ተጫዋች በተጠናቀቀው የ2025/26 የፕሪምየር ሊግ ውድድር ዘመን ለኤቨርተን በ32 ጨዋታዎች ተሰልፎ 6 ግቦችን በማስቆጠር እና 3 ግቦች እንዲቆጠሩ አመቻችቶ በመስጠት ጥሩ ጊዜ ያሳለፈ ሲሆን፣ በቅርቡ በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ለሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን በ3 ጨዋታዎች 1 ግብ እና 2 አሲስት በማድረግ ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል። ሆኖም ኤቨርተን ለተጫዋቹ ከፍተኛ የዝውውር ዋጋ በመጠየቁ እና የቶፊሶቹ አሰልጣኝ ዴቪድ ሞየስ ተጫዋቹን የመሸጥ ፍላጎት የሌላቸው በመሆኑ፣ ዝውውሩ በቀላሉ እንዳይጠናቀቅ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። በሌላ በኩል ጃክ ግሪሊሽ ወደ ኤቨርተን መመለስ እንደሚፈልግ ማሳወቁ ሁኔታዎችን ሊቀይራቸው እንደሚችል ተጠቁሟል። የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን የክንፍ መስመር ተጫዋች ጃክ ግሪሊሽ ከሰንደርላንድ እና ከልጅነት ክለቡ አስቶን ቪላ የቀረቡለትን የዝውውር ጥያቄዎች ውድቅ በማድረግ ወደ ኤቨርተን ለመመለስ መወሰኑን ለማንቸስተር ሲቲ አሳውቋል። በተጠናቀቀው የ2025/26 የውድድር ዘመን በዴቪድ ሞየስ ስር በውሰት በኤቨርተን ያሳለፈው ግሪሊሽ፣ በጥር ወር በገጠመው የእግር ጉዳት ምክንያት የውድድር ዘመኑ ቀድሞ እስከተጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ በ22 ጨዋታዎች 2 ጎሎችን በማስቆጠር እና 6 አሲስቶችን በማመቻቸት ጥሩ ብቃት ማሳየት ችሎ ነበር። ተጫዋቹ ከጉዳቱ ለማገገም በኤቨርተን የልምምድ ማዕከል ለመቆየት መወሰኑም ከክለቡ ጋር ያለውን ጠንካራ ቁርኝት የሚያሳይ ነው። በአሁኑ ወቅት ሁለቱ ክለቦች በሚያደርጉት ድርድር ማንቸስተር ሲቲዎች ኢሊማን ንዲያዬን በጥብቅ ስለሚፈልጉት፣ ግሪሊሽን እና ተጨማሪ ገንዘብ በመክፈል የተጫዋቾች ልውውጥ (Swap deal) ለማድረግ እየተነጋገሩ ይገኛሉ። ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ያለው ኮንትራት የመጨረሻ ዓመት ላይ የሚገኘው ግሪሊሽ፣ በቋሚነት ወይም በውሰት ውል ወደ ኤቨርተን የመመለስ ስምምነቱ ይጠበቃል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ