ነሐሴ 08 ቀን 2018 (መናኸሪያ ሬዲዮ) በታሪክ ውስጥ ከተሠሩት እጅግ አነጋጋሪ እና ያልተለመዱ የፊልም ሥራዎች መካከል የሳዳም ሁሴን ፕሮጀክት የሆነው «ክላሽ ኦፍ ሎያልቲስ» (Clash of Loyalties) ወይም በአረብኛ «አል-መሰአላ አል-ኩብራ» (ታላቁ ጥያቄ) የተሰኘው ፊልም ይጠቀሳል።
የዛሬ 40 ዓመታት ገደማ (በፈረንጆቹ የ1980ዎቹ መጀመሪያ) ሳዳም ሁሴን የኢራቅ ፕሬዚደንት ሆኖ ሥልጣን ላይ እንደወጣ፣ አገሩ የብሪታንያን ቅኝ ግዛት ቀንበር ስትታገል የሚያሳይ ታላቅ ታሪካዊ ፊልም ማዘጋጀት ፈልጎ ነበር። ይህንን ሀሳብ እውን ለማድረግም ከሆሊዉድ ድንቅ ሥራዎች ጋር የሚመጣጣን ግዙፍ በጀት መድቦ፣ ዓለም አቀፍ የፊልም ከዋክብትን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሰሜናዊ በረሃዎች አሰማራ።
ፊልሙን ለመሥራት ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ግን አንድ አስደንጋጭ ክስተት ተፈጠረ፤ ሳዳም ሁሴን ከጎረቤቷ ኢራን ጋር ደም አፋሳሽ ጦርነት ጀመረ። ነገር ግን የኢራቁ መሪ የመደበውን በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር አግዶ ፕሮጀክቱን ለማስቆም ፈቃደኛ አልነበረም። በዚህም የተነሳ ከብሪታንያ እና ከሌሎች የዓለም ክፍሎች የመጡት ተዋናዮች፣ ዳይሬክተሮች እና የፊልም ባለሙያዎች ከዚህ ቀደም ከሚያውቁት ሰላማዊ የሥራ አካባቢ ፈጽሞ በተለየ መልኩ፣ በዙሪያቸው እውነተኛ ሚሳኤሎች እና ቦምቦች እየፈነዱ በከፍተኛ ሥጋት ውስጥ ሆነው ቀረጻውን እንዲያከናውኑ ተገደዱ።
የወቅቱ ተዋናዮች በኋላ ላይ ሲያስታውሱት፦ «እኛ የለመድነው እንደ ሼፐርተን፣ ፓይንዉድ ወይም ሆሊዉድ ባሉ ሰላማዊ ስፍራዎች ፊልም መስራት ነበር እንጂ፣ በየአቅጣጫው እውነተኛ ሚሳኤሎች እና ቦምቦች እየፈነዱ ባሉበት ባዶ በረሃ ውስጥ መሆንን አይደለም። ወደ አገሪቱ ስንገባም አውሮፕላናችን የተዋጊ ጀቶች ታጅቦ በጨለማ ውስጥ ነበር ያረፈው፤ ነገሮች የተለመዱ እንዳልሆኑ የተረዳንበት ቅጽበት ነበር» ብለዋል።
ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ደግሞ በቀረጻ መካከል ድንገት አንዳንዶች ኢራቃውያን ተዋናዮች ከቀረጻ ስፍራ ይጠፉ ነበር፤ ምክንያቱም ለጦርነት ግንባር ተጠርተው ወደ ጦር ሜዳ ይወሰዱ ነበር። በወቅቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስም የገነባው እንግሊዛዊው ተዋናይ ኦሊቨር ሪድ (Oliver Reed) በፊልሙ ላይ ዋናውን ገጸ-ባህሪ ተጫውቷል። ፊልሙ ተጠናቆ ለዕይታ ቢበቃም፣ በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ሁኔታ እና ሳዳም ሁሴን በፈጸማቸው ፖለቲካዊ ቀውሶች የተነሳ ዓለም አቀፍ የስርጭት ፈቃድ ሊያገኝ አልቻለም። ለረጅም ዓመታትም ተረስቶ በብሪታንያ በሚገኝ አንድ ጋራዥ ውስጥ ተቀምጦ ቆይቷል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ