ነሐሴ 15 ቀን 2018 (መናኸሪያ ሬዲዮ) ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች የልደት፣ የጋብቻ፣ የፍቺ እና የሞት ወሳኝ ኩነቶቻቸውን በመደበኛው የምዝገባ ስርዓት በማስመዝገብ ህጋዊ እውቅናና ጥበቃ ማግኘት መጀመራቸውን ያስታወቀው የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ነው፡፡
አገልግሎቱ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2019 ያሻሻለችውን የስደተኞች አዋጅ ቁጥር 1110/2011 መሠረት በማድረግ፣ በስደተኞች መብት አያያዝ ዙሪያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሻጋሪና ዘመናዊ የተባለለትን የህግ ማዕቀፍ እየተተገበረ መሆኑን ገልጿል።
መናኸሪያ ሬዲዮ ያነጋገራቸው የአገልግሎቱ የዋና ዳይሬክተር አማካሪ አቶ ዘውዱ በዳዳ እንደገለጹት፣ ስደተኞች የመንቀሳቀስ፣ ንብረት የማፍራት፣ የስራ ዕድል፣ የትምህርት፣ የጤና እና የባንክ አገልግሎት እንዲሁም የመንጃ ፈቃድና የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አገልግሎቶችን የማግኘት መብታቸውን ለማስከበር እየተሰራ ይገኛል።
ለአዋጁ አተገባበር በበጎ ከሚጠቀሱት መካከል የስደተኞች የስራ መብት መመሪያ አንዱ ሲሆን፣ ስደተኞች ተቀጥረው ወይም በራሳቸው ስራ ፈጥረው እንዲንቀሳቀሱ እድል ያመቻቸላቸው እንደሆነም ገልጸዋል።
በሌላ በኩል፣ በቅርቡ ስራ ላይ የዋለው የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ስደተኞችን አካታች ባደረገ መልኩ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
አሰራሩ መዲናዋን ጨምሮ በሁሉም የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎችና ማረፊያዎች እየተተገበረ እንዳለም አስረድተዋል፡፡ ይህም ስደተኞች መደበኛ የባንክ፣ የቴሌኮም፣ የትምህርት፣ የጤና እና የፋይናንስ አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ እንደሚያግዛቸው አብራርተዋል።
እንዲሁም ስደተኞች የልደት፣ የጋብቻ፣ የፍቺ እና የሞት ኩነቶቻቸውን በመደበኛው የኢትዮጵያ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስርዓት በማስመዝገብ ህጋዊ ማስረጃ ማግኘት መጀመራቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የሚገኙ ስደተኞች በአማካይ ከ15 እስከ 30 ዓመታት የቆዩ እንዳሉም አገልግሎቱ ገልጿል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ