ሰኔ 01 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) በዩናይትድ ስቴትስ፣ በታሪክ ትልቁ የተባለውና በኦፕሬሽን “ኤፒክ ፉሪ” (Operation Epic Fury) የጀመረው የኢራን ጦርነት፣ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቁጥጥር ውጪ እየሆነ መምጣቱን የሚያሳዩ አዳዲስ ክስተቶች በጎላ ሁኔታ እየታዩ ነው። ትራምፕ ሁለቱም ወገኖች ወደ ሰላም ስምምነት ተቃርበዋል በማለት በተደጋጋሚ ቢገልጹም፣ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማስቀጠልና ቀውሱን ለመግታት የሚደረገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ከፍተኛ ፈተና ውስጥ ወድቋል ነው የተባለው።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ እንዲፈርስ ከፍተኛ ስጋት የፈጠረው፣ የትራምፕን ጥሪ ወደ ጎን በመተው የተፈጸመው አዲስ ጥቃት ነው። ሄዝቦላህ በእስራኤል ሰሜናዊ ክፍል ላይ ያካሄደውን የሮኬት ጥቃት ተከትሎ፣ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ “በምንም መልኩ የአጸፋ ጥቃት እንዳይሰነዝሩ” በስልክ በቀጥታ ለማሳወቅና ውጥረቱን ለማርገብ ጥረት አድርገው ነበር። ሆኖም የእስራኤል ጦር የትራምፕን ልመናና ማሳሰቢያ ውድቅ በማድረግ፣ በኢራን መካከለኛና ምዕራባዊ ክፍሎች በሚገኙ ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ አስደንጋጭ የአየር ጥቃት መፈጸሙን ይፋ አድርጓል።
ይህ የእስራኤል እርምጃ በዋይት ሀውስ እና በቴል አቪቭ መካከል ያለውን ከፍተኛ የፖለቲካ ውጥረት የገለጠ ሲሆን፣ ትራምፕ ጦርነቱን ለመምራትና ቀጠናውን ለማረጋጋት ያላቸውን አቅም ጥያቄ ውስጥ ጥሎታል። በሌላ በኩል የኢራን ፓርላማ አፈ-ጉባኤ በሰጡት መግለጫ፣ ከአሁን በኋላ በአካባቢው የሚገኙ ማናቸውም የጥምር ጦሩ እና የአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈሮች ለኢራን “ህጋዊ የጥቃት ኢላማ” መሆናቸውን በይፋ አስታውቀዋል።
ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለአሜሪካ ወታደራዊ በጀት ብቻ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እያስወጣ ሲሆን፣ የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ መዘጋትና በነዳጅ ማውጫዎች ላይ የደረሰው ጉዳት ዓለም አቀፍ የኤኮኖሚ ቀውስ አስከትሏል። ትራምፕ ሁኔታው ወደ ከፋ ቀጠናዊ ጦርነት እንዳያመራ ስጋት ቢገባቸውም፣ በእስራኤል እና በኢራን መካከል የሚካሄደው የአጸፋ ጥቃት አዙሪት የአሜሪካን ተሰሚነት ክፉኛ እየፈተነው ይገኛል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ