በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና በሚቀጥሉት ውጥረቶች፣ የሰላም እጦት እና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት በኢትዮጵያ መጠለያ ያገኙ ስደተኞች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሀገራቸው የመመለስ ተስፋቸው እጅግ እየመነመነ መጥቷል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከ34 ሀገራት የተፈናቀሉ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል 41 በመቶ የሚሆኑት ከጎረቤት ደቡብ ሱዳን የጦርነት እና የግጭት እሳት ሽሼው የመጡ ናቸው።
እነዚህ ስደተኞች በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ በአማካይ እስከ 15 ዓመታት፣ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ደግሞ ከ30 ዓመታት በላይ ለማለፍ መገደዳቸውን የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት (RSA) መረጃዎች ያሳያሉ። መናኸሪያ ሬዲዮ ያነጋገራቸው የአገልግሎቱ የዋና ዳይሬክተር አማካሪ አቶ ዘውዱ በዳዳ እንደሚሉት፣ ለዓመታት ሲተገበር የቆየው ጊዜያዊ የሕይወት አድን እርዳታ የስደተኞችን ህይወት በዘላቂነት ሊለውጥ አልቻለም። ይልቁንም የዕለት እርዳታን በመጠበቅ የተወሰነ ህይወት እንዲመሩ በማድረግ የምርታማነት አቅማቸውን ገድቦታል፡። በተለይም አሁን ባለው ሁኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚመደበው በጀት በፍጥነት እየቀነሰ በመምጣቱ፣ ስደተኞችን በጊዜያዊ እርዳታ ብቻ ተስፋ አስሮ ማቆየት በአስተናጋጇ ሀገር ላይም ከባድ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና እየፈጠረ ይገኛል። በመሆኑም አሰራሩ ስደተኞች ባላቸው ክህሎትና ሙያ ተሰማርተው ራሳቸውንና አካባቢውን የሚጠቅሙበት ዘላቂ የልማት አሰራር ላይ ማተኮር እንዳለበት አቶ ዘውዱ ያሰምሩበታል።
ይህ የስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር በተለይ በጎረቤት የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ከባድ ጫና ፈጥሯል። በጋምቤላ ክልል ብቻ የሚጠለሉ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ቁጥር ከ400 ሺህ ማለፉንና ይህም በክልሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ ጫና ማሳደሩን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡጅሉ ጊሎ ገልጸዋል። በድጋፍ እጦትና በጸጥታ ችግሮች ምክንያት ስደተኞች ከመደበኛው ነዋሪ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ በመሆኑ ጉዳዩ የፌዴራል መንግስቱን ልዩ ትኩረት እንደሚፈልግም ተናግረዋል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነጎ በበኩላቸው፣ በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን ያለው አለመረጋጋት በፍጥነት የሚቆም ባለመሆኑ የስደተኞች ፍሰቱ ወደፊትም ሊቀጥል እንደሚችል በመጠቆም ዘላቂ የመፍትሔ አቅጣጫዎች መቀየስ እንዳለባቸው አሳስበዋል። ከደቡብ ሱዳን በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ከ112 ሺህ በላይ፣ እንዲሁም በአፋር ክልል ከ62 ሺህ በላይ ስደተኞች በከባድ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ።

በሌላ በኩል፣ ከሀገር የሚወጡ ዜጎች በሚያጋጥሟቸው ስቃዮች ዙሪያ አስደንጋጭ መረጃዎች እየወጡ ነው። የንጋት ግሎባል ኢኒሼቲቭ መስራች አቶ ዳንኤል መሰለ እና የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጄ ተግይበሉ እንደሚሉት፤ በህገ-ወጥ መንገድና በባሕር አቋርጠው በሚሰደዱ ዜጎች ላይ ከጽኑ የእስራትና የባርነት እንግልት ባሻገር የአካል ክፍሎችን የመስረቅ (Organ Trafficking) ዘግናኝ ወንጀሎች እየተፈጸሙባቸው ይገኛል። የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ተመራማሪዋ ሀና ወልደኪዳን ባካሄዱት ጥናት ደግሞ፣ ከተለያዩ ሀገራት ተመልሰው መደበኛ የስራ ዕድል ያላገኙ ዜጎች 30 በመቶ የሚሆኑት እንደገና ለአደገኛ የደጋግሞ ስደት መንገድ ለመጋለጥ እንደሚገደዱ አረጋግጠዋል።
እነዚህን ውስብስብ ሰብዓዊ ችግሮች ለመቋቋም ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2019 ያሻሻለችውን የስደተኞች አዋጅ ቁጥር 1110/2011 መሠረት በማድረግ የተሻሉ ህጋዊ መብቶችን ተግባራዊ ለማድረግ እየሞከረች ነው። አቶ ዘውዱ በዳዳ እንደሚያብራሩት፣ ስደተኞች ተቀጥረው ወይም በራሳቸው ስራ ፈጥረው እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል መመሪያ ከመውጣቱ በላይ የመንቀሳቀስ፣ ንብረት የማፍራት፣ በትምህርትና ጤና የመሳተፍ እንዲሁም የባንክ እና የመንጃ ፈቃድ አገልግሎት የማግኘት መብቶቻቸው እንዲከበሩ እየተሰራ ነው። በተጨማሪም ስደተኞችን አካታች ያደረገው የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት በመዲናዋ እና በሁሉም የመጠለያ ጣቢያዎች በመተግበሩ፣ ስደተኞች እንደ ልደት፣ ጋብቻ፣ ፍቺ እና ሞት ያሉ ወሳኝ ኩነቶቻቸውን በመደበኛው ስርዓት አስመዝግበው ህጋዊ እውቅና እና የፋይናንስ አገልግሎት ማግኘት ጀምረዋል።
በጌታሁን አስናቀ
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ