መስከረም 07 ቀን 2019ዓ.ም.(መናኸሪያ ሬዲዮ) በመዲናዋ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተጠቃሚ ያላቸው ነገር ግን ከአውቶቡስ ውጭ ምድብተኛ የሆነ የታክሲ አገልግሎት የሌላቸው ተርሚናሎች በርካታ መሆናቸውን በአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳኛቸው ሽፈራው ለጣቢያችን ገልጸዋል፡፡ ቢሮው በነባር ተርሚናሎችና በአዲስ መልክ በተመሰረቱ ተርሚናሎች የማህበረሰቡን ፍላጎት ያማከለ የጥናት ስራ ባለፉት 3 ወራት በመስራት፣ የሕዝብ ፍላጎት ያለባቸው እንዲሁም ከአውቶቡስ እና ከደረጃ 1 የሕዝብ ተሽከርካሪዎች በተጨማሪ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚያስፈልጋቸው በርካታ ቦታዎችን በተደረገው ጥናት መሰረት መለየት መቻሉን አስታውቀዋል፡፡ በጥናቱ መሰረት በተለያዩ ምክንያቶች የትራንስፖርት አገልግሎት የሌለባቸው 46 መስመሮች በአዲስ መልኩ እንዲከፈቱ፣ እንዲሁም 12 መስመሮች ደግሞ ከነበራቸው ተርሚናል እንዲራዘሙ የማድረግ ስራ በዚህ ዓመት መጀመሩን አቶ ዳኛቸው ገልጸዋል፡፡ ከጀሞ መገናኛ፣ ከጀሞ ሜክሲኮ፣ ከመገናኛ ጎሮ እንዲሁም ከጎሮ ቦሌ ከህብረተሰቡ በደረሱት ጥቆማዎች መሰረት ተደጋጋሚ ጥናት ተደርጎባቸው ለማስጀመር በሂደት ላይ ያሉና የጀመሩ መስመሮች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ከፍተኛ የትራንስፖርት ተጠቃሚ ያላቸው፣ በስፋት ከታሪፍ ውጭ የሚከፈልባቸው፣ ሕግ የሚጣስባቸውና የህብረተሰብ እንግልት ያለባቸው አካባቢዎችን በቀጣይ በመለየት ጥናት እንደሚደረግ ቢሮው አስታውቋል፡፡
___
ሀሳብ እና‘ሳ‘ፍራለን
ምላሽ ይስጡ