የቤት ግንባታን ሙሉ በሙሉ እየቀየረ ያለው አዲሱ የእንጨት ብሎኬት ነሐሴ 30 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የቤት ግንባታ ሲታሰብ ቀድሞ ወደ አእምሮ የሚመጣው የሲሚንቶ፣ አሸዋ እና ድንጋይ ውህደት ነው። ነገር ግን ይህ ባህላዊና ብዙ ጊዜ የሚወስድ አሰራር በአዲሱ የቴክኖሎጂ ፈጠራ እየተተካ ይመስላል። አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ መነጋገሪያ የሆነውና እንደ ህፃናት መጫወቻ እርስ በእርስ የሚገጣጠመው የእንጨት ብሎኬት የግንባታን አለም ሙሉ በሙሉ እየቀየረው ይገኛል። ይህ ፈጠራ የተለመደውን የሲሚንቶ ብሎኬት በመተካት፣ ያለ ምንም ውኃ፣ አሸዋ እና ሲሚንቶ አጠቃቀም በደረቁ የቤት ግድግዳን በጥቂት ቀናት ውስጥ ሰርቶ ለማጠናቀቅ ያስችላል። እነዚህ ብሎኬቶች በፋብሪካ ደረጃ በከፍተኛ ጥራት ከተቀነባበሩ እንጨቶች የተሰሩ ሲሆን፣ በውስጣቸው ሙቀትና ቅዝቃዜን የሚከላከል ቁሳቁስ ይዘው ይዘጋጃሉ። ብሎኬቶቹ እርስ በእርስ የሚቆለፉ በመሆናቸው አሰራራቸው የተወሳሰበ የግንባታ ሙያ አይጠይቅም። ቦታቸው ላይ ለማስቀመጥና ለማጠባበቅ የሚያስፈልገው የላስቲክ መዶሻ ብቻ ሲሆን፣ ከተደረደሩ በኋላ በውስጣቸው በሚያልፉ የእንጨት ወይም የብረት ዘንጎች እርስ በእርስ ተያይዘው የታሰሩ በመሆናቸው ለቤት ግድግዳ የሚሆን ጠንካራ መዋቅር ይፈጥራሉ። የዚህ ቴክኖሎጂ ጥቅሞች በርካታ ናቸው። በወራት የሚቆጠርን የኮንክሪትና የሲሚንቶ ማድረቂያ ጊዜ በማስቀረት፣ የአንድን ቪላ ቤት ሙሉ ግድግዳ ከሶስት እስከ አምስት ባሉት ቀናት ውስጥ ሰርቶ ለማጠናቀቅ ያስችላል ነው የተባለው። ከባድ ማሽነሪዎችን እና በርካታ የሰራተኛ ኃይልን ስለማይፈልግ የግንባታ ወጪን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል። በተጨማሪም የሲሚንቶ ምርት የሚያስከትለውን ከፍተኛ የካርበን ልቀት በማስቀረት ለአካባቢ አየር ንብረት ተስማሚ የሆነ አሰራርን ያቀርባል። በብሎኬቱ ውስጥ ያለው የመከላከያ ንብርብር በቤቱ ውስጥ ያለውን የሙቀት መጠን ስለሚቆጣጠር፣ ለቅዝቃዜና ለሙቀት ማሞቂያ የሚወጣውን የኤሌክትሪክ ኃይል ይቆጥባል። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራትና በአውስትራሊያ ለቪላዎች፣ ለተጨማሪ ክፍሎችና ለአነስተኛ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በስፋት እየዋለ የሚገኘው ይህ ቴክኖሎጂ፣ ወደፊት የሲሚንቶን የበላይነት በከፊል ሊተካ እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያዎች ይገምታሉ።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ