ነሐሴ 26 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) ብዙዎቻችን ጠዋት ስንነሳ ስልካችንን ከፍተን የዕለቱን የአየር ሁኔታ በቀላሉ እንመለከታለን። ነገር ግን በዚያች “ዛሬ ዝናብ ይዘንባል” ወይም “ፀሐያማ ይሆናል” የምትል አጭር መረጃ ጀርባ፣ በዓለማችን ላይ ያሉ እጅግ ግዙፍ ሱፐር-ኮምፒውተሮች በቢሊዮን፣ አልፎ ተርፎም በትሪሊዮን የሚቆጠሩ የሒሳብ ስሌቶችን እንደሚያከናውኑ ያውቁ ነበር? ይህ ሂደት የሚጀምረው ኮምፒውተሩ መላውን ዓለም እና ከባቢ አየር “ግሪድ” በሚባሉ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ትናንሽ ምናባዊ ሳጥኖች በመከፋፈል ነው። በመቀጠል በእያንዳንዱ ሳጥን ውስጥ ያለውን የሙቀት መጠን፣ የነፋስ ፍጥነት እና የአየር እርጥበት ከሳተላይቶች፣ ከራዳሮች እና ከአየር ሁኔታ ጣቢያዎች ይሰበስባል። ከዚህ በኋላ አየር እና ደመናዎች ወደፊት እንዴት እንደሚንቀሳቀሱ ለማወቅ በእያንዳንዱ ሳጥን ውስጥ ባለው መረጃ ላይ የፊዚክስ ቀመሮችን ይተገብራል። ኮምፒውተሩ በቀጥታ ወደ ነገ መዝለል ስለማይችል፣ በመጀመሪያ ከ1 ደቂቃ በኋላ፣ በመቀጠል ከ2 ደቂቃ በኋላ የሚሆነውን እያለ ለ24 ሰዓታት ሙሉ ደጋግሞ ያሰላል። በአጭሩ፣ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሳጥኖች ላይ እነዚህን መረጃዎች ደቂቃ በደቂቃ ለማስላት በቢሊዮን የሚቆጠሩ እና ከዚያ በላይ የሒሳብ ስሌቶች በአንድ ጊዜ መከናወን አለባቸው። በመሆኑም ስልካችን ላይ የምናያት አጭር የአየር ሁኔታ መረጃ የዚህ ሁሉ ግዙፍ የሳይንስ ውጤት ነች።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ