በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የዴሞክራሲ ባህልን ለማሳደግና በፖለቲካዊ እንዲሁም ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ፍጭት እንዲኖር ከሚሰሩ የመወያያ መድረኮች መካከል አንዱ የ”ሀበ-ጋር የክርክር መድረክ” ይገኝበታል።
ፕሮግራሙ ላለፉት ሶስት ዓመታት በዋና ዋና ሀገራዊና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ የቆየ ቢሆንም፣ በቂ የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ በማጣቱ ምክንያት ለጊዜው ስራዎቹን አቁሞ እንደሚገኝ ያስታወቁት የሀበ-ጋር የፕሮግራም አስተባባሪ ዘላለም ወዳጅ ናቸው።
እንደ አስተባባሪው ገለጻ፣ የሀበ-ጋር የክርክር መድረክ ወደ አሁኑ የፖለቲካና የሰብአዊ መብት መወያያ መድረክነቱ ከመሸጋገሩ በፊት፣ ለተከታታይ አምስት ዓመታት የተማሪዎችና የወጣቶችን የክርክር ብቃት የሚያጎለብቱ ዝግጅቶችን ሲያቀርብ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በኋላም ባለፉት ሶስት እና አራት ዓመታት ገደማ በአዲስ አበባ ከተማ ትኩረቱን በፖለቲካ፣ በሕግ ባለሙያዎችና በሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች ውይይት ላይ በማድረግ በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ትኩረትን ማግኘት የቻለ ቢሆንም፣ ስፖንሰር የሚያደርጉ አካላትን ማግኘት አዳጋች መሆኑ በስራው ላይ ጫና ማሳደሩንም አብራርተዋል።
ይሁን እንጂ መድረኩ ለጊዜው ቢቋረጥም፣ እስካሁን የተካሄዱት በርካታ አከራካሪና አስተማሪ ውይይቶች ሳይባክኑ በስርዓት ተሰንደው የተቀመጡ መሆኑ ተገልጻል። የተካሄዱት ክርክሮች በሙሉ በምስልና በድምጽ ተቀርጸው በዩቲዩብ፣ በቲክቶክ እና በሌሎች የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ለህዝብ ክፍት ከመሆናቸውም በላይ፣ ለወደፊት ተመራማሪዎችና ለሚዲያ ባለሙያዎች በማህደር (Archive) ደረጃ በቢሮ ተደራጅተው እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።
ተቋሙ መደበኛ የክርክር መድረኩን እስኪጀምር ድረስ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
ምላሽ ይስጡ