ሰኔ 19 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን መሠረታዊ ችግሮች በምክክር ለመፍታት ስታደርገው የነበረው ጥረት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱ ይታወቃል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለረጅም ጊዜያት በሀገሪቱ ከሚገኙ ሁሉም ክልሎች፣ እንዲሁም በውጭ ሀገራት ከሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ 2 ሺህ የሚደርሱ አጀንዳዎችን ማሰባሰቡንና ከእነዚህም ውስጥ 8 የሚሆኑ ሀገራዊ አጀንዳዎችን መለየቱን አስታውቋል።
ከሂደቱ ጀምሮ ተሳታፊ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህንን አስመልክቶ ለመናኸሪያ ሬዲዮ በሰጡት አስተያየት፤ ለዋናው ጉባኤ በኮሚሽኑ የተመረጡት አጀንዳዎች ሀገራዊ ጉዳዮችን መሠረት ያደረጉና የእነሱንም ጥያቄ ያካተቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ከጅምሩ ተሳትፎ ሲያደርግ መቆየቱን ያስታወሱት የፓርቲው ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ራሄል ባፌ፤ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ የሚቀርቡት 8 አጀንዳዎች በውስጣቸው ሰፊ ሐሳብ የያዙ፣ የኅብረተሰቡን ጥያቄ የሚወክሉ ብሎም ሀገራዊ ጉዳዮች እንዳይዘለሉ ለማካተት የተሞከረባቸው ናቸው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
በዋናነት በ8 ምድብ የተቀመጡት አጀንዳዎች የፖለቲካ፣ የመንግሥት አደረጃጀት፣ የሰላም ግንባታ እና ሌሎችም እጅግ ወሳኝ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ ይዞ የተነሳው ዓላማ ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ችግር በምክክር መፍታት በመሆኑ፣ ሀገራዊ አጀንዳዎች በግልጽ ተለይተው መቀመጣቸው ውይይቱን ምቹ እንደሚያደርገው የገለጹት ደግሞ የህዳሴ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ የማነ አሰፋ ናቸው።
በሂደቱም እንደ ፓርቲ ያቀረቧቸው አጀንዳዎች በሀገራዊ አጀንዳነት መካተታቸውን በመጥቀስ፤ ይህም ኮሚሽኑ ከበርካታ አጀንዳዎች መካከል ለሀገራዊ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠቱን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል። እንደ ሀገር ያልተግባባንባቸውን ጉዳዮች ለመነጋገር ወስኖ ሂደቱን ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ማድረስ መቻሉ እጅግ ትልቅ ስኬት መሆኑን በመጥቀስ፣ ለጉባኤውም በፓርቲያቸው በኩል ተሳትፎ ለማድረግ እየተዘጋጁ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሐምሌ 8 ቀን ጠቅላላ ጉባኤውን እንደሚያካሂድ መግለጹ ይታወሳል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ