ግንቦት 18 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)የሚኒስትሮች ምክር ቤት ግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ.ም ባካሄደው 55ኛ መደበኛ ስብሰባው ሀገራዊ ኢኮኖሚን፣ ማኅበራዊ ልማትንና ዘላቂ መረጋጋትን ታሳቢ ባደረጉ ልዩ ልዩ የሕግ ማዕቀፎች፣ ፖሊሲዎችና የብድር ስምምነቶች ላይ በሰፊው ተወያይቶ ሙሉ ድምፅ ያላቸውን ውሳኔዎች አሳልፏል።
ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በሁለት የውጭ የፋይናንስ ድጋፍና የብድር ስምምነቶች ላይ ነው። የመጀመሪያው ለአርብቶ አደር ምግብና የኑሮ ዘይቤ ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል ከአፍሪካ ልማት ባንክ የተገኘ የ46 ሚሊዮን 300 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ብድር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ለስድስተኛው ምዕራፍ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ከዓለም ዓቀፍ የልማት ማኅበር የተገኘ የ146 ሚሊዮን 100 ሺህ ኤስ ዲ አር (SDR) የብድር ስምምነት ነው። ሁለቱም ስምምነቶች ከሀገሪቱ የብድር አስተዳደር ፖሊሲ ጋር መጣጣማቸው ተረጋግጦ ይጸድቁ ዘንድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ተወስኗል።
በታክስና በንግድ ዘርፍ ዘመናዊ አሠራርን ለመዘርጋት የቀረቡ ማሻሻያዎችም የምክር ቤቱን ይሁንታ አግኝተዋል። በዚህም መሠረት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ለውጦች ከዘመናዊ ዓለም አቀፍ አሠራሮች ጋር ለማጣጣም፣ የታክስ አለመግባባቶችን በሰላማዊና ፍትሐዊ መንገድ ለመፍታትና ግልጸኝነትን ለማስፈን የተዘጋጀው የፌዴራል ታክስ አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመርቷል። በተመሳሳይ የወጪ ንግድ በግብርና ምርቶች ላይ ያለውን ጥገኝነት ለማላቀቅና ፍትሐዊ የንግድ ሥርዓትን ለመዘርጋት የወጣው የኢትዮጵያ የንግድ ረቂቅ ፖሊሲ የጸደቀ ሲሆን፣ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣንን አደረጃጀትና ሥልጣን ለመወሰን የቀረበው ማሻሻያ ረቂቅ ደንብም በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን ተወስኗል።
የግብርናውን ዘርፍ ከተለምዶአዊ አሠራር ወደ ቢዝነስ መር ሥርዓት ለማሸጋገር፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የአነስተኛ አምራቾችን የመደራደር አቅም ለማሳደግ የተዘጋጀው የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ ረቂቅ አዋጅ በስፋት ከተገመገመ በኋላ ግብዓቶች ታክለውበት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ተደርጓል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከሥርዓተ ምግብ መዛባት ጋር የተያያዙ በሽታዎች በሀገር ኢኮኖሚና ምርታማነት ላይ የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ ለመቀነስ የሚያስችለው የምግብ ሥርዓት እና ሥርዓተ ምግብ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ተመርቷል።
በአረንጓዴ ልማትና በስታቲስቲክስ ዘርፍ የተዘጋጁ አዳዲስ ረቂቅ አዋጆችም ቀርበው ውሳኔ አግኝተዋል። የኢትዮጵያን የካርበን ገበያ ስትራቴጂ ወደ ተግባር ለመለወጥ፣ ለአረንጓዴ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠርና ከካርበን ንግድ የሚገኘው ገቢ በአልሚዎችና በአካባቢው ማህበረሰብ መካከል በፍትሐዊነት የሚከፋፈልበትን ሥርዓት ለመደንገግ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ የካርበን ገበያ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ተወስኗል። የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ሞያዊ ነፃነትን ለማረጋገጥና የመረጃ ምስጢራዊነትን ለመጠበቅ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅም በተመሳሳይ ሁኔታ ለፓርላማ ተልኳል።
በኢነርጂ፣ በኢንሹራንስና በስርዓተ ጾታ እኩልነት ዙሪያ የቀረቡ ፖሊሲዎችና አዋጆችም በምክር ቤቱ ታይተዋል። የሀገሪቱን የኢነርጂ ሀብት በአነስተኛ ዋጋ በማልማት ዘላቂና አስተማማኝ አቅርቦት ለመፍጠር የተዘጋጀው የኢነርጂ ረቂቅ ፖሊሲ እንዲሁም ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከላከልና ልዩ ትኩረት ለሚሹ ሴት አካል ጉዳተኞች ምላሽ ለመስጠት የተዘጋጀው ብሔራዊ የሴቶች ማብቃት እና የስርዓተ ጾታ እኩልነት ረቂቅ ፖሊሲ ከጸደቁበት ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆኑ ተወስኗል። የኢንሹራንስ ገበያውን ተዓማኒነትና መረጋጋት ለማጠናከር የወጣው የኢንሹራንስ ረቂቅ አዋጅም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተላልፏል።
በመጨረሻም ምክር ቤቱ በሁለት ደንቦች ላይ ተወያይቶ አፅድቋል። በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብንና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ለማስፈጸም የቀረበው በሕግ የሰውነት መብት የተሰጣቸው አካላት ተጠቃሚ የሚሆኑ ባለቤቶችን መረጃ ግልጸኝነት ለመደንገግ የወጣው ረቂቅ ደንብ ጸድቋል። እንዲሁም ለራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ከመንግሥት የሚሰጠውን የበጀት ድጋፍ ሥርዓት ባለው ጥቅል በጀት ላይ የተመሠረተ ለማድረግ፣ የፋይናንስ ተጠያቂነትንና ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ የወጣው ረቂቅ ደንብ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን በሙሉ ድምፅ ፅድቋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ