ሚያዚያ 12 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አቅም ያሳድጋል የተባለውና ከዛሬ ሚያዝያ 12 እስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም. የሚቆየው የኢትዮጵያ – አውሮፓ ህብረት የንግድ ፎረም 2026 በአዲስ አበባ ከተማ ተጀምሯል። “የግሎባል ጌትዌይ አቅምን መጠቀም” በሚል መሪ ቃል የተጀመረው ይህ ፎረም በተለይ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አቅም የሚያሳድግ መሆኑን በጉባኤው መክፈቻ ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰመሬታ ሰዋሰው ተናግረዋል።
በጉባኤው ላይ ከ500 በላይ የአውሮፓና የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ተገኝተዋል። መድረኩ በሁለቱ አካላት መካከል ያለውን የንግድና የኢንቨስትመንት ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል። በጉባኤው ላይ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ስምምነቶች እንደሚፈረሙ የተገለጸ ሲሆን፣ ከሚጠበቁት ስምምነቶች መካከል የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ሴክሬታሪያት እና የአውሮፓ ህብረት የ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዩሮ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ፎረሙ በዋናነት በኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ሥርዓት ላይ አዎንታዊ ለውጥ ሊያመጡ በሚችሉ ዘርፎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ በመድረኩ ተገልጿል። የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ተደራሽነትና የሁለትዮሽ ግንኙነትን የሚያጠናክር ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ በተለይም በታዳሽ ኃይል፣ በአረንጓዴ ኢነርጂ ኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ እና ዲጂታላይዜሽን፣ በግብርና እና በምግብ ዋስትና፣ በግብርና ምርት ማቀነባበር እና የገበያ ትሥሥር፣ በዘመናዊ ትራንስፖርት እንዲሁም በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ትስስርና ስምምነት ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል።
አክለውም የኢትዮጵያ – አውሮፓ ህብረት የንግድ ፎረም 2026፣ የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የቆየ የኢኮኖሚ ትብብር በማሳደግና አዳዲስ የኢንቨስትመንት ስምምነቶችን ለማቀድ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል። በጉባኤው ላይ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታን እና የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽነርን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የልማት ፋይናንስ ተቋማት፣ ባለሀብቶችና የንግድ ምክር ቤቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ። በተጨማሪም በተመረጡ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ የፓናል ውይይቶችና የንግድ ትስስር መድረኮች በመካሄድ ላይ ናቸው።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ