መስከረም 05 ቀን 2019ዓ.ም.(መናኸሪያ ሬዲዮ) በመዲናዋ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ዙሪያ ማንኛውንም ተሽከርካሪ ደርቦ ማቆም በጥብቅ እንደሚያስቀጣ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታወቀ። በመዲናዋ የትምህርት ቤቶች መከፈትን ተከትሎ የትራፊክ ፍሰት መጨናነቅ ከወትሮው በተለየ መልኩ እንደሚስተዋል የሚናገሩት የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ ገነት ዲባባ፤ በትምህርት ቤቶች መግቢያና መውጫ ሰዓት ተሽከርካሪን በዋና መንገዶች ላይ ደርቦ ማቆም 1 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ ተናግረዋል። በግል ተሽከርካሪ ወደ ትምህርት ቤት ይጓጓዙ የነበሩ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ሰርቪስ እንዲጓዙ ከትምህርት ቤቶች ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል። ወላጆች ተሽከርካሪን መንገድ ላይ ለሰከንዶች አቁመው ተማሪዎችን ማውረድ እንደሚችሉ አያይዘው የተናገሩት ዳይሬክተሯ፤ ነገር ግን ተሽከርካሪን ለደቂቃዎች በአካባቢው ማቆምም ሆነ አቁሞ መውረድ ግን እንደማይቻል አስታውቀዋል። በየዓመቱ ከ500 እስከ 1 ሺህ የሚደርሱ የበጎ ፈቃደኛ ተማሪዎችን በትራፊክ ማስተናገድ ሥራ ላይ በማሰልጠን በትምህርት ቤቶች አካባቢ ተማሪዎችንና ማህበረሰቡን የማስተናገድ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን ወ/ሮ ገነት አስታውሰዋል። እነዚህ በጎ ፈቃደኞች በትምህርት ቤቶች አካባቢ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲሰጡ ይደረጋል ብለዋል። ባለሥልጣኑ ከትምህርት ቤት አመራሮች፣ ከወላጅ ኮሚቴዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ጥብቅ የቁጥጥርና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ማከናወኑን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል። በትምህርት ቤት መግቢያና መውጫ ሰዓት ላይ መንገድ ዘግተው ተሽከርካሪ በሚያቆሙና ተማሪዎችን በሚያወርዱና በሚጭኑ አሽከርካሪዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግና ሕግ ተላልፈው የሚገኙት እንደሚቀጡ ዳይሬክተሯ አመላክተዋል።
___
ሀሳብ እና‘ሳ‘ፍራለን
ምላሽ ይስጡ