ሰኔ 10 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የፀሐይ ብርሃን ጠልቆ ጨለማ በሰፈነበት የምሽት ሰዓት፣ እንደ ልብ የፀሐይ ኃይል ማመንጨት የሚቻልበት ዓለም ቢፈጠር ምን ሊሰማዎት ይችላል? ሳይንስ ፊክሽን የሚመስለውን ይህንን ሃሳብ እውን ለማድረግ “ሪፍሌክት ኦርቢታል” (Reflect Orbital) የተሰኘው የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ተቋም በጠፈር ላይ ግዙፍ መስተዋቶችን በማሰማራት በምሽት “የፀሐይ ብርሃንን ለመሸጥ” የሚያስችል ታላቅ እቅድ ይዞ ብቅ ብሏል።
ተቋሙ “ኤሬንዲል-1” (Earendil-1) የተሰኘችውን የ18 ሜትር የሙከራ ሳተላይት ወደ ጠፈር ለማስወንጨፍ በዝግጅት ላይ ይገኛል። ዋናው እቅዱ ግን 54 ሜትር ስፋት ያላቸው ግዙፍ መስተዋቶች የተገጠሙላቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ ሳተላይቶችን ወደ ምድር ምህዋር ማስገባት ነው። እነዚህ መስተዋቶች በቀን እና በሌሊት መገናኛ መስመር ላይ በመሆን፣ የፀሐይን ብርሃን በቀጥታ በምድር ላይ ወደሚገኙ የሶላር ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ያንፀባርቃሉ። ዓላማውም በቀን ከምናገኘው ከፍተኛ የፀሐይ ብርሃን 20 በመቶ ያህሉን በምሽት በማቅረብ፣ ንጹህ የሶላር ኃይል ሳይቋረጥ 24 ሰዓት ሙሉ እንዲመረት ማድረግ ነው።
ነገር ግን ነገሩ በተግባር መስራት መቻሉ ላይ የፊዚክስ ሊቃውንት ትልቅ ጥያቄ እያነሱ ነው። የፀሐይ ብርሃን ከሩቅ ጠፈር ተነስቶ ምድር ላይ ሲያርፍ በራሱ በሰፊው የመበተን ባህሪ አለው። በዚህም ምክንያት አንድ የጠፈር መስተዋት የሚፈጥረው የብርሃን ክበብ በምድር ላይ ቢያንስ 7 ኪሎ ሜትር ስፋት የሚኖረው ሲሆን፣ የሚሰጠው የብርሃን መጠን ግን ከቀኑ የፀሐይ ብርሃን 15 ሺህ እጥፍ ያነሰ እና የደበዘዘ ይሆናል። ከዚህም በላይ ሳተላይቶቹ በሰከንድ 7.5 ኪሎ ሜትር በሆነ ከፍተኛ ፍጥነት ሰማዩን ስለሚቀዝፉ፣ አንድ መስተዋት ከአንድ የሶላር ጣቢያ በላይ መቆየት የሚችለው ለ3.5 ደቂቃዎች ብቻ ነው። ስለዚህ ለምሳሌ ለአንድ ሰዓት ያህል ተከታታይ ብርሃን ለማግኘት ብቻ እርስ በእርስ የተቀናጁ በሺዎች የሚቆጠሩ ሳተላይቶች ያስፈልጋሉ።
ይህ እቅድ በሳይንስ ማህበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ እና ስጋት እየቀሰቀሰ ይገኛል። የስነ-ፈለክ ተመራማሪዎች እነዚህ መስተዋቶች ሆን ተብሎ የሚፈጠር “የብርሃን ብክለት” (Light pollution) የሚያስከትሉ በመሆናቸው፣ በሰማይ ላይ ሙሉ ጨረቃ ከምትሰጠው በላይ ከፍተኛ ደመቅ ያለ ብርሃን ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ያስጠነቅቃሉ።
ይህ ደግሞ በምድር ላይ ያሉ ስሱ የቴሌስኮፕ መመርመሪያዎችን እስከመሰባበር እና ከዋክብትን የመታዘብ ሂደትን ሙሉ በሙሉ ለማደናቀፍ እንደሚችል ተገልጿል። የኩባንያው መሥራቾች ብርሃኑ ለአጭር ጊዜ እና ከትላልቅ የምርምር ማዕከላት ውጭ የሚሆን ነው ቢሉም፣ ተቺዎች ግን በዱር እንስሳት ስነ-ህይወት ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተፅዕኖ እና ለንግድ ትርፍ ሲባል የተፈጥሮን የምሽት ሰማይ ማበላሸት ተገቢ አለመሆኑን በመጥቀስ ሞገስ አልሰጡትም።
የከዋክብትን ውበት የሚያስጣፋን ከሆነ፣ በፈለጉት ሰዓት “የፀሐይ ብርሃንን በቅናሽ ማዘዝ” የሚለውን አማራጭ ይቀበሉታል? የጠፈር መስተዋት ክርክር አሁንም በአለማቀፍ ደረጃ ቀጥሏል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ