ነሐሴ 26 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና ውጤትን በተመለከተ በተማሪዎች የሚቀርቡ ቅሬታዎች ታይተው ምላሽ እየተሰጠባቸው መሆኑን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል። የዘንድሮው ዓመት የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና 60 በመቶው በኦንላይን፣ ቀሪው ደግሞ በወረቀት እንዲሰጥ ተደርጎ ውጤቱም ለሁሉም ተፈታኞች እንዲደርስ መደረጉን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር እሸቱ ከበደ ተናግረዋል። የፈተናው ውጤት መለቀቅ ተከትሎ ተፈታኞች ቅሬታቸውን እያቀረቡ እንደሚገኙ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ተቋሙ ቅሬታዎችን በመቃኘት ምላሽ እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። የፈተና ውጤት ማነስ፣ በፈተና ወቅት በየዕለቱ አቴንዳንስ አለመሙላት እና ሌሎችም ቅሬታዎች በተፈታኞች በኩል እየቀረቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል። አገልግሎቱ ቅሬታዎችን በልዩ ሁኔታ እየተመለከተ ለእያንዳንዱ ቅሬታ ተገቢው ምላሽ እንዲሰጥ እያደረገ መሆኑን የገለጹት ዶክተር እሸቱ፣ “ውጤቴ አነሰ” በሚል ለተቋሙ ከገቡት ቅሬታዎች መካከል እስካሁን ማስተካከያ የሚያስደርግ አንድም አለመገኘቱን አመልክተዋል። በተጨማሪም በውጤቱ ላይ ቅሬታ ያላቸው ሌሎች ተፈታኞች ቅሬታቸውን ለተቋሙ እንዲያቀርቡ ጥሪ አስተላልፈዋል። በ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ የመልቀቂያ ፈተና ከተፈተኑ 550 ሺሕ ተፈታኞች መካከል 76 ሺሕ 544 ተማሪዎች ማለፋቸውን የትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ