
ሰኔ 01 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. የተከናወነውን የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ መስጠት ሂደት ተከትሎ፣ በአሁኑ ሰዓት ከተለያዩ የምርጫ ክልሎች ወደ ማዕከል በመምጣት ላይ ያሉ ውጤቶችን የማረጋገጥና የማጣራት ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ እያከናወነ እንደሚገኝ ይፋ አድርጓል።
ቦርዱ በአሁኑ ወቅት ውጤቶችን የማረጋገጥ፣ የኦዲት ግኝት ያለባቸውን የምርጫ ውጤቶች የመመርመር እንዲሁም የተረጋገጡትን መረጃዎች ወደ ማዕከላዊ የመረጃ ቋት የማስገባት ተግባራትን በልዩ ትኩረት እያከናወነ ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ በፖለቲካ ፓርቲዎችና በግል ዕጩዎች የቀረቡ አቤቱታዎችን በሕግ ባለሙያዎች ጉባዔ አማካኝነት የማደራጀትና የምሥክር የመሥማት ሥራ እየተሠራ ሲሆን፣ እነዚህን ሂደቶች ያጠናቀቁ የምርጫ ውጤቶች ለቦርዱ ውሣኔ ቀርበው ከፀደቁ በኋላ በሕጉ መሠረት ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረጉ ተገልጿል።
በሌላ በኩል ቦርዱ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያና በወታደራዊ ካምፖች ልዩ የምርጫ ጣቢያዎችን በማቋቋም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ እንዲሣተፉ መራጮችን መመዝገቡን አስታውሷል። ይህ ልዩ የምዝገባ ሂደት የተከናወነው “በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 17” ለቦርዱ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ነው።
በመሆኑም በእነዚህ የልዩ ጣቢያዎች ካምፖች ውስጥ በመራጭነት የተመዘገቡ ዜጎች ድምፅ የመስጠት ሂደት በነገው ዕለት ሰኔ 2 ቀን 2018 ዓ.ም. በተደራጀ መልኩ የሚከናወን እንደሚሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ