ነሐሴ 30 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) ኢምባሲዎች የየሀገራቸውን ባህል በማስተዋወቅ የፌስቲቫሉ አካል እንዲሆኑ እየሰሩ እንደሚገኙ የጳጉሜን ፌስቲቫል አዘጋጆች ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታወቁ። በዋናነት አፍሪካዊ አንድነትንና ትስስርን ለማጠናከር የኢትዮጵያን ዘመን አቆጣጠር የአፍሪካም ለማድረግ እየሰሩ እንደሚገኙ በመግለጽ፣ ከዚሁ ዓላማ ጎን ለጎን የባህል ትስስርን ለመፍጠር ከኢምባሲዎች ጋር እየሰሩ እንደሚገኙ የጳጉሜን ፌስቲቫል ማኅበር ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይለአብ መረሳ ለጣቢያችን ተናግረዋል። የአፍሪካውያንን ባህል በጋራ በማቅረብና በማሳየት በኩል፣ የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ኢምባሲዎቻቸውን ተጠቅመው እንዲሰሩ ለማስቻል ከዘንድሮው 9ኛው የጳጉሜን ፌስቲቫል ጀምሮ ስምምነት ላይ ለመድረስ እየተሰራ ይገኛልም ተብሏል። አፍሪካውያን ጳጉሜን እንደ አንድ የጋራ መድረክ በመጠቀም እንዲያከብሩት ፌስቲቫሉ ከወዲሁ ሥራዎችን እየሰራና በየዓመቱ እየወተወተ ይገኛል ሲሉም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል። የጳጉሜን ቀናት ማኅበረሰቡ በተነሳሽነትና በአዲስ መንፈስ ወደ አዲሱ ዓመት የሚሸጋገርበት እንዲሆን ሕዝባዊና መንግሥታዊ እውቅናን ለማጠናከር የፊርማ ማሰባሰብ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ