መስከረም 06 ቀን 2019ዓ.ም.(መናኸሪያ ሬዲዮ)በከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት እና ሥራ ፕሮጀክት አማካኝነት ተደራራቢ የአካል ጉዳት ያለባቸውን፣ በጽኑ ሕመም ምክንያት አልጋ ላይ የዋሉ አረጋውያንንና ዕድሜያቸው ለሥራ ሳይደርስ የቤተሰብ አስተዳዳሪ የሆኑ ሕፃናትን ጨምሮ ለ94 ሺህ 527 ዜጎች ሁለገብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለመናኸሪያ ሬድዮ አስታውቋል፡፡ ድጋፉ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች ለሚኖሩ 48 ሺህ 108 አባወራዎች እንደሆነ የሚናገሩት የቢሮው የማኅበራዊ ሴፍቲኔት እና ኑሮ ማሻሻያ ዳይሬክተር አቶ ቢንያም ግርማ፤ ለአባወራዎቹ በወር 589 ብር የገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ አንድ አባወራ እስከ አራት የቤተሰብ አባላትን ማካተት እንደሚችል የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ ከገንዘብ ድጋፉ በተጨማሪም ከከተማው ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ነፃ የጤና መድህን አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን አቶ ቢንያም ገልጸዋል፡፡ ቢሮው ከመንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት የምግብ፣ የአልባሳት፣ የቤት ማደስና መኖሪያ ቤት የማመቻቸት ድጋፍ እያደረገ እንደሆነና ባለሙያዎች ቤት ለቤት በመዘዋወር የሥነ-ልቦና ድጋፍ እየሰጡ እንደሆነ ጠቁመዋል። ፕሮግራሙ ከተጀመረበት ከዘጠኝ ዓመታት ወዲህ በሙከራ ደረጃ ከነበሩት 16 ሺህ ተጠቃሚዎች ተደራሽነቱን በማስፋት ለ94 ሺህ 527 ዜጎች ሁለገብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ዳይሬክተሩ አመላክተዋል፡፡
___
ሀሳብ እና‘ሳ‘ፍራለን
ምላሽ ይስጡ