ሚያዚያ 06 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) አርሰናል በዚህ ክረምት ከፍተኛ ተስፋ የሚጣልባቸውን የወጣት አካዳሚ ተጫዋቾቹን ኤታን ንዋኔሪን እና ማይልስ ሉዊስ ስኬሊን ለሽያጭ ለማቅረብ መዘጋጀቱ ተሰምቷል። ሳሚ ሞክቤልን ጨምሮ የተለያዩ ምንጮች እንደዘገቡት፣ ክለቡ ለሁለቱ ተጫዋቾች በድምር 100 ሚሊዮን ፓውንድ የሚጠጋ ዋጋ ተምኗል። አርሰናል እነዚህን የሀሌ ኤንድ (Hale End) ውጤቶች ለመሸጥ የወሰነው ከሽያጩ የሚገኘው ገቢ በፕሪምየር ሊጉ የፋይናንስ ደንብ (PSR) መሰረት እንደ “ሙሉ ትርፍ” (pure profit) ስለሚቆጠርና የክለቡን የፋይናንስ አቅም ለማጠናከር ስለሚረዳ ነው ተብሏል።
ኤታን ንዋኔሪ በዘንድሮው የ2018 (2025/26) የውድድር ዘመን በአርሰናል ቤት በሁሉም ውድድሮች 12 ጨዋታዎችን አድርጎ 2 ግቦችንና 3 አሲስቶችን አስመዝግቧል። በተለይም በሊግ ካፕ ድንቅ ብቃቱን ቢያሳይም፣ በፕሪምየር ሊጉ በቋሚነት የመሰለፍ ዕድል ለማግኘት ተቸግሯል። ያንን ተከትሎ ባለፈው ጥር ወር ወደ ኦሎምፒክ ማርሴ በውሰት ማቅናቱ ይታወሳል። በቀድሞው አሰልጣኝ ሮቤርቶ ዲ ዜርቢ ስር ጥሩ የመሰለፍ ዕድልና በራስ መተማመን አግኝቶ የነበረው ንዋኔሪ፣ አሰልጣኙ ተሰናብተው አዲሱ አሰልጣኝ ሀቢብ ባዬ ክለቡን ከተረከቡ በኋላ ግን ተቀያሪ ወንበር ላይ ለመቀመጥ ተገዷል። በዚህ አሰልጣኝ ስር እስካሁን አንድም ጨዋታ ማድረግ አልቻለም።
ማይልስ ሉዊስ ስኬሊ በበኩሉ በዘንድሮው የውድድር ዘመን 8 ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን፣ በአማካይ በጨዋታ 89 በመቶ የተሳካ ኳስ የማቀበል ስኬትና 1.5 ኳሶችን በመንጠቅ ረገድ ጥሩ አፈፃፀም አሳይቷል። ሁለቱም ተጫዋቾች በቅርቡ የረጅም ጊዜ ኮንትራት ቢፈርሙም፣ የሌሎች የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ፍላጎትና የአርሰናል የፋይናንስ ስሌት ከክለቡ እንዲለቁ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ይጠበቃል።
ክለቡ ንዋኔሪንና ሉዊስ ስኬሊን በመሸጥ የሚያገኘውን 100 ሚሊዮን ፓውንድ እንደ ዩሊያን አልቫሬዝ ያሉ ውድ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ሊጠቀምበት እንደሚችል ይገመታል። ይሁን እንጂ ደጋፊዎች ክለቡ የወደፊት ተስፋ የሆኑትን ወጣቶች ለመሸጥ ማቀዱን በስጋት እየተመለከቱት ይገኛሉ። በተለይም ኤታን ንዋኔሪ በክለቡ ታሪክ በፕሪምየር ሊግ የተሰለፈ ትንሹ ተጫዋች መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣ የእሱ መልቀቅ በአካዳሚው ውጤቶች ላይ ትልቅ ክፍተት ሊፈጥር ይችላል የሚሉ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።
ሁለቱም ተጫዋቾች በፕሪሚየር ሊግ ክለቦች እየተፈለጉ ይገኛሉ። ማንቸስተር ዩናይትድ የሉዊስ ስኬሊ ፈላጊ ሆነው ብቅ ሲሉ፣ የሰሜን ለንደኑ ተቀናቃኝ ቶተንሃም ደግሞ የኤታን ንዋኔሪ ፈላጊ ሆኗል። ማንቸስተር ዩናይትድ ቀደም ሲል ቺዶ ኦቢ ማርቲንና አይደን ሄቨን የተባሉ የሀሌ ኤንድ ውጤቶችን ማስፈረሙ የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ የግራ መስመር ተከላካይ ቦታቸውን ለማጠናከር በሉዊስ ስኬሊ ላይ ትኩረት አድርገዋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ