ነሐሴ 07 ቀን 2018 (መናኸሪያ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የሚገኙ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ለበርካታ ዓመታት የሚሰጡት የአጭር ጊዜ ሰብዓዊ እርዳታና የሕይወት አድን ድጋፍ ዘላቂ መፍትሔ ባለመሆኑ፣ አሰራሩ ወደ ልማታዊ ድጋፍ ሊቀየር እንደሚገባው የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት አስታውቋል።
በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የሚገኙ ስደተኞች በአማካይ እስከ 15 ዓመታት፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ከ30 ዓመታት በላይ በመጠለያ ጣቢያዎች እንደሚቆዩ ያስታወቁት በተቋሙ የዋና ዳይሬክተር አማካሪ አቶ ዘውዱ በዳዳ ናቸው።
ጊዜያዊ ሰብዓዊ እርዳታ ብቻ መደረጉ የስደተኞችን ሕይወት ማሻሻልና የሚጠበቀውን ለውጥ ማምጣት አለመቻሉን ገልጸዋል። በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሰብዓዊ እርዳታ የሚመደበው የበጀት ድጋፍ በፍጥነት እየቀነሰ መሆኑን አስታውቀዋል።
በመሆኑም ለልማታዊ ፋይናንስና ዘላቂ አሰራር ትኩረት መስጠት እንደሚገባ በመግለጽ፤ ይህ የልማት አሰራር ተግባራዊ ሲደረግ ስደተኞች ብቻ ሳይሆኑ የአካባቢው ተወላጆችም በጋራ ተጠቃሚ እንደሚሆኑበት ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ይተገበር የነበረው አሰራር ስደተኞች በመጠለያ ጣቢያ ተቀምጠው የዕለት እርዳታ እንዲጠብቁ የሚያደርግ እንጂ ምርታማነታቸውን የሚያበረታታ እንዳልሆነ የተናገሩት አቶ ዘውዱ፤ ስደተኞች ባላቸው ሙያ፣ በንግድ ሥራና ክህሎት ተሰማርተው ራሳቸውን እንዲሁም የሚያስተናግዳቸውን ማኅበረሰብ እንዲጠቅሙ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት በቀጠናው ባለው የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የሰላም እጦት፣ ረኃብና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ምክንያት ስደተኞች በፍጥነት ወደ ሀገራቸው የመመለስ ዕድላቸው አነስተኛ መሆኑን አስረድተዋል። በመሆኑም ስደተኞችን ለረጅም ጊዜ በመጠለያ ጣቢያ አስቀምጦ መደገፍ በአስተናጋጇ ሀገር ላይ ከባድ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጫና እየፈጠረ እንዳለ ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ 1.2 ሚሊዮን ስደተኞችን እያስተናገደች መሆኑን አገልግሎቱ አስታውቋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ