ሐምሌ 22 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከሰሞኑ ባዘጋጀው በተፋሰስ ምክር ቤት ረቂቅ ደንብ ዙሪያ በተካሄደው የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ላይ፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ የውሃ ሀብት አስተዳደር ከግብፅና ሱዳን ባሻገር የሀገር ውስጥ የግጭት መንስኤ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ከምግብና መስኖ ውሃ አጠቃቀም፣ ከመጠጥ ውሃና ከሌሎች በውሃ ዙሪያ ካሉ ፍላጎቶች ከፍተኛነት የተነሳ አሁን ላይ ከሁሉም ክልሎች ጥያቄዎች እየተነሱ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይም በላይኛውና በታችኛው ተፋሰስ ክልሎች መካከል የግጭት መንስኤ ሲሆን ማየታቸውን ጠቅሰው፣ አሁንም ዘላቂ መፍትሔ ካልተገኘለት አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ከግብፅና ከሱዳን ከሚነሱ ውዝግቦች ባሻገር፣ በሀገር ውስጥ በውሃ ሀብት አስተዳደር ምክንያት ግጭቶች እንዳይፈጠሩ በሀገር ውስጥ የውሃ አጠቃቀም አስተዳደር ላይ ከፍተኛ ሥራ ይጠበቃል ሲሉ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢ በሚባል ደረጃ በውሃ ሀብት የታደለች እንደመሆኗ፣ በሀገር ውስጥ የውሃ አስተዳደር ላይ በቂ ሥራ ሊሠራ እንደሚገባ ሀሳባቸውን የሰጡት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ተደራዳሪና የመካከለኛው ምስራቅ አጥኚ ፕሮፌሰር አደም ካሚል ናቸው።ያሉንን 8 ሀይቆችና ከ12 በላይ ወንዞች በአግባቡ ብንጠቀም የሚያጋጩን ችግሮች ሁሉ ይቀረፋሉ፤ ያሉን የውሃ ሀብቶች ለሁሉም የሚበቁ በመሆናቸው በአግባቡ በማልማትና በመጠቀም ሁሉም ዜጋ እንዲያገኝ ማድረግ ይቻላል ብለዋል።
በመጨረሻም ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብት ሁሉም ዜጋ በእኩል አልምቶ እንዲጠቀም ማድረግ እንደሚገባ ተመላክቷል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ