ሰኔ 01 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የንግድ ስርዓት በደረሰኝ የመገበያየት ልማድ ሰፊ ክፍተት እንደሚታይበትና፥ በሸማቹም ሆነ በነጋዴው ማህበረሰብ ዘንድ ደረሰኝ መጠቀም እንደ ኋላ ቀር አሰራር እንደሚታይ የተናገሩት የህግ ባለሙያ እና ጠበቃው አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ ናቸው።
ይህ አይነቱ ክፍተት ነጋዴዎች ያለአግባብ እንዲበለጽጉ፥ በአንጻሩ መንግስት ደግሞ ማግኘት የሚገባውን የገቢ ግብር እንዲያጣ እያደረገው ነው ብለዋል።
ይህን ችግር ለመቅረፍ በታክስ አስተዳደር አዋጅ ላይ የተደረገው ማሻሻያ ተገቢና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን መሆኑን የተናገሩት ባለሙያው፥ ሆኖም አሰራሩ ለሙስና ተጋላጭ እንዳይሆን ጥብቅ ቁጥጥር መደረግ እንዳለበት እና ለተቆጣጣሪዎችም አሳሪ የህግ ማዕቀፍን ማካተት እንደሚገባ አመላክተዋል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ በበኩላቸው፥ በአጠቃላይ በአፍሪካ አገራት በአግባቡ ግብር ባለመሰብሰቡ ምክንያት በየዓመቱ 4 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደሚያጋጥም ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያም ከእርዳታና ብድር ጥገኝነት ወጥታ አቅሟን እንድታደራጅ የደረሰኝ ግብይትን አስገዳጅ የሚያደርገው ህግ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚገባ ያነሳሉ።
ይህ አሰራር በአግባቡ ስራ ላይ መዋሉ ነጋዴው ህግን እንዲያከብርና እንዲፈራ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ፥ ለሀገር ኢኮኖሚ ሁለንተናዊ ጠቀሜታ እንዳለው ነው የገለጹት።
ከሰሞኑ ማንኛውም ነጋዴ ለሸማቹ ምንም አይነት ደረሰኝ የማይሰጥ ከሆነ በእያንዳንዱ ደረሰኝ ብዛት ከ100 ሺህ ብር ጀምሮ የቅጣት እርምጃ የሚጥል ረቂቅ አዋጅ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ መመራቱ ይታወቃል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ