ሚያዚያ 06 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)የሊቨርፑል እና የፓሪስ ሴንት ዠርሜን (PSG) የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ የመልስ ጨዋታ ዛሬ ምሽት በአንፊልድ ስታዲየም ይከናወናል። በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ፒኤስጂ በዲዚሬ ዱዌ እና በክቪቻ ክቫራትስኬሊያ ግቦች 2 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል። በዚህም ምክንያት ሊቨርፑል ወደ ግማሽ ፍፃሜው ለማለፍ በዛሬው ጨዋታ ቢያንስ የሦስት ግብ ልዩነት ማሸነፍ ይጠበቅበታል።
ፒኤስጂ በዘንድሮው የሻምፒዮንስ ሊግ 36 ግቦችን በማስቆጠር እና 259 የጎል ሙከራዎችን በማድረግ (ከእነዚህም ውስጥ 96ቱ ኢላማቸውን የጠበቁ ናቸው) እንዲሁም በተጋጣሚ የግብ ክልል ውስጥ 486 የኳስ ንክኪዎችን በማድረግ በውድድር ዘመኑ ቀዳሚው ክለብ ሆኖ ይገኛል። ሊቨርፑል ባለፈው ሳምንት 2 ለ 0 ሲሸነፍ አንድም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ አለመቻሉ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህም ከስድስት ዓመት በኋላ (ከ2020-21 የውድድር ዘመን ከሪያል ማድሪድ ጋር ከነበረው ጨዋታ በኋላ) ለመጀመሪያ ጊዜ ያጋጠመ ክስተት ነው።
የፒኤስጂው ክቫራትስኬሊያ በ4 ተከታታይ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ላይ ጎል ማስቆጠር የቻለ የመጀመሪያው የክለቡ ተጫዋች መሆን ችሏል። የኦፕታ ሱፐር ኮምፒውተር ትንበያ ሊቨርፑል በሜዳው የማሸነፍ 39.6 በመቶ ዕድል ሲሰጠው፣ ፒኤስጂ ደግሞ 37.9 በመቶ ዕድል አግኝቷል። ይሁን እንጂ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ሰፊው ዕድል (85.8 በመቶ) የፒኤስጂ ሲሆን፣ የሊቨርፑል ዕድል 14.2 በመቶ ብቻ ነው። ሆኖም ሊቨርፑል በ2019 ከባርሴሎና ጋር በነበረው ጨዋታ 3 ለ 0 ተሸንፎ በአንፊልድ 4 ለ 0 በመመለስ ውጤት የመቀልበስ ታሪክ ያለው መሆኑ ለደጋፊዎቹ ተስፋ ሰጥቷል።
ከቡድን ዜናዎች ጋር በተያያዘ፣ ባለፈው ቅዳሜ ፉልሃምን 2 ለ 0 ሲያሸንፉ ግብ ያስቆጠሩት መሐመድ ሳላህ እና ወጣቱ ሪዮ ንጉሞሃ ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸው ተገልጿል። በተለይም የ17 ዓመቱ ንጉሞሃ በአንፊልድ ጎል ያስቆጠረ የሊቨርፑል ታሪክ ትንሹ ተጫዋች በመሆን ክብረ ወሰን ሰብሯል። በሻምፒዮንስ ሊጉ 28 የጎል ዕድሎችን በመፍጠር ቀዳሚ የሆነው ፍሎሪያን ቪርትዝም ለዛሬው ጨዋታ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።
ፒኤስጂ በበኩሉ ብራድሊ ባርኮላን እና ኩዌንቲን ንጃንቱን በጉዳት ምክንያት የማያሰልፍ ሲሆን፣ የፋቢያን ሩዊዝ መሰለፍ ደግሞ አጠራጣሪ ነው። አችራፍ ሀኪሚ በዛሬው ጨዋታ የሚሰለፍ ከሆነ በክለቡ ታሪክ 55 የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎችን በማድረግ የአንሄል ዲ ማሪያን እና ኤዲንሰን ካቫኒን ክብረ ወሰን ይጋራል። በሊቨርፑል በኩል አሊሰን ቤከር ከጉዳቱ ባለማገገሙ የመሰለፍ ዕድሉ ጠባብ ሲሆን፣ ተተኪው ግብ ጠባቂ ማማርዳሽቪሊ ባለፉት 15 ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር የወጣው በሦስቱ ብቻ መሆኑ ለክለቡ አሳሳቢ ሆኗል።
ጨዋታው ምሽት 4:00 ሲጀምር ጣልያናዊው ዳኛ ማውሪዝዮ ማሪያኒ በመሀል ዳኝነት ይመሩታል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ