የወንጀል መከላከል ዘርፉን ለማዘመንና ህበረተሰቡ በቀላሉ ለፖሊስ ጥቆማ እንዲሰጥ ለማስቻል ስራ ላይ የዋለው የሞባይል መተግበሪያ ወይም የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የዜጎች መተግበሪያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዱባይ በተደረገ ውድድር ምርጥ የፖሊስ መተግበሪያ (Best Police Application) በመባል አንደኛ መውጣቱን የፌዴራል ፖሊስ ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል፡፡
በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የቴክኖሎጂ ማስፋፋያ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ደምሴ ይልማ በትላንትናው እለት ለ116ኛ ጊዜ በተከበረው የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ክብረ በዓል የመዝጊያ ስነ ስርዓት መረጃው ለህዝብ ይፋ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
አሁን ላይ የፌዴራል ፖሊስ ሁሉን አቀፍ የአቅም ግንባታ እያደረገ ይገኛል ያሉት ኮማንደር ደምሴ በቴክኖሎጂው ዘርፍ በተሰሩ ስራዎች በጎ ውጤቶች መታየት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ጊዜያት በመተግበሪያው የቀረቡ ጥቆማዎችን መነሻ በማድረግ ህግ የማስከበር፤ ወንጀለኞችንም ለህግ የማቅረብ ስራ መሰራቱን ኮማንደሩ አስረድተዋል፡፡
ወንጀሎች ድንበር ተሻጋሪ እንደመሆናቸው መጠን ከሌሎች ሀገራት ጋር ትብብር በመፍጠር የቁጥጥር ስራዎችን ለመስራት የሚያስችሉ የቴክኖሎጂና የሰው ኃይል ዝግጁነት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ኮማንደር ደምሴ ገልጸዋል፡፡
116ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ምሥረታ ቀን የመዝጊያ ፕሮግራም በትላንትነው እለት በመስቀል አደባባይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተከብሯል፡፡
__
ምላሽ ይስጡ