
ኢትዮጵያ የመንግሥት አስተዳደር በመመስረት፣ ሕግና ሥርዓት በማበጀት፣ በሃይማኖት መታነጽ፣ በጀግንነት ሀገርን መጠበቅ እንዲሁም ማኅበራዊ ቁርኝት በማጥበቅ ለሺህ ዘመናት የኖሩ ታላላቅ ሕዝቦች ያሉባት ሀገር ናት፡፡ ታሪኳ ሲነበብ እልፍ አኩሪ ገድሎች ይዘረዘራሉ። የአፍሪካ የነፃነት ቀንዲል የሆነው ማንነቷም ከድል፣ ከክብርና ከእፁብ ድንቅ እሴቶች የተሸመነ መኾኑ ይመሰክራል።
በረዥሙ የሀገርነት ታሪካችን የተፈጠሩ የሀሳብ አለመግባባቶች ግን አንድ ቦታ ላይ ያልተጠገነ ስብራት ፈጥረውብናል። ይኸውም ልዩነቶችን በኃይል የመፍታት ልማድ ነው። ከጠመንጃ አፈሙዝና ከእርስ በርስ የግጭት አዙሪት ያልተላቀቀው ሕዝብ ዛሬ ላይ አብዝቶ የሚፈልገው መሠረታዊ ነገር ሰላም ሆኗል፡፡ ዛሬ ላይ የተጓዝንባቸው መንገዶች ክፉኛ አቁስለውናል። ትርክቶች ሥር ሰድደው አጋጭተውናል። ይህን አድካሚ ጉዞ ለማገት የጋራ ውይይት ማድረግ ዋነኛው መንገድ መሆኑ ሀቅ ነው፡፡
የኢትዮጵያውያን የዘመናት ያለመግባባት ችግርን በንግግር እንፍታ የሚለው ሐሳብ ከአራት ዓመታት በፊት መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዓለ ሲመት በተከበረበት ዕለት ተሰማ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በወቅቱ እንዳሉት፤ “ኢትዮጵያ የዘመናት ችግሮቿን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሰላምን በሚወዱና ውይይትን በሚያስቀድሙ ልጆቿ ትፈታዋለች፤ ለዚህ ደግሞ የብልጽግና መንግሥት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንዲቋቋም እገዛ ያደርጋል” ነበር ያሉት።
በመስቀል አደባባይ የተሰማው የምክክር ሐሳብ አሁን ላይ በመዲናዋ አዲስ አበባ ከተለያዩ አካባቢዎች በመጡ ተወያዮች በኮንቬንሽን ሴንተር በይፋ ተጀምሯል፡፡ የተለያዩ ሀገራት በፖለቲካዊ ሽግግር፣ ከእርስ በርስ ግጭት በኋላ ወይም ሰፊ የሀገር ውስጥ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ሀገራዊ ምክክሮችን (National Dialogue) አካሂደዋል። ኢትዮጵያም የዚህ ጉዞ አካል ለመሆን “ኢትዮጵያ እየመከረች ነው” በሚል መሪ ቃል ሁለተኛውን ምዕራፍ የምክክር ሂደት ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ከ4 ሺህ በላይ ተሳታፊዎችን በመጥራት ጀምራለች፡፡ አምስት መቶ ሰዎችን የሚይዙ 8 ቡድኖች ተዋቅረው፣ ለሀገራዊ መግባባት እና የዘመናት ቁርሾን ለመቅረፍ ነጥረው በወጡ ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ዙሪያ መምከር ጀምረዋል፡፡
በባህል፣ በቋንቋ፣ በአኗኗር ዘይቤና በእምነት የማይገናኙ እነዚህ አራት ሺህ ተወያዮች በተለያዩ ክፍሎች በአንድ ጣሪያ ሥር ማደር ከጀመሩ 8 ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ ይህ ሁነት በብሔር ልዩነት ለምትታመሰው ኢትዮጵያ ትልቅ ማሳያ የሚሆን ቤተሰባዊነትን መስርቷል፡፡
አባ ገዳ ቃበቶ ኤደቦ ይባላሉ፤ የመጡት ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ነው፡፡ ባለፉት ስምንት ቀናት ከተለያዩ ወገኖች ጋር ያደረጉትን ቤተሰባዊነት ሲመለከቱ “ለምን የብሔር ልዩነታችን ያለመግባባታችን ምክንያት ሆነ?” ብለው ራሳቸውን እንደጠየቁ ለመናኸሪያ ሬዲዮ ተናግረዋል።
“አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ የሚለው እሳቤ ብሔርን ለመጥራት ሳይሆን ልዩነታችንን ለማጉላት ሲውል ነበር” የሚሉት ከማዕከላዊ ጎንደር ጫልጋ ወረዳ የቅማንት ብሔረሰብን ወክለው የመጡት የሃይማኖት መምህር አማረ ሙሉነህ ናቸው። በቆይታቸው የጋራ ማንነታቸውን በዚች በትንሿ ክፍል ውስጥ መመልከታቸውን ይገልጻሉ።
ትናንት በመክፈቻው የነበሩት ሂደቶችና የቀረቡት መልእክቶች ጥያቄ ይዞ ለመጣ ተሳታፊ ትልቅ ትምህርት የሚሰጡና አንዲት ኢትዮጵያን ዳግም በመገንባት ሂደት ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዳለው አመላካች መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመጡት ሼህ ኡመር ሙስጠፋ ናቸው።
ትናንት የተካሄደውን የመክፈቻ ፕሮግራም ጨምሮ ባለፉት 8 ቀናት የነበረው ቆይታ እና ሂደት ለምክክሩ ትልቅ መደላደል የፈጠረ መሆኑን ከወላይታ ሶዶ ዞን የመጡት መጋቢ ሳሙኤል ሳና ተናግረዋል። አብዛኞቹ ሂደቶች ወደ አንድነት የሚያመጡና የሚያቀራርቡ እንዲሁም ቀጣዮቹን ጊዜያት የቤተሰባዊነት ምክክር ለማድረግ የሚያስችሉ መሆናቸውንም ገልጸዋል ።
ከኦሮሚያ ክልል ሴቶችን በመወከል በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ሲሳተፉ ያገኘናቸው ወ/ሮ አበበች አበራ በበኩላቸው፤ በቋንቋ፣ በባህል፣ በአኗኗርና በሃይማኖት የሚለያዩ ተሳታፊዎች በሕብረ-ብሔራዊ አንድነት መንፈስ በአንድ ጣሪያ ሥር እያደሩ ምክክሩን በራሱ መንገድ ጀምረውታል ይላሉ።

ወ/ሮ ኢማም መሐመድ ይባላሉ፤ የሐረሪ ክልል አስፈጻሚ አካልን ወክለው በሀገራዊ ምክክሩ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ ባለፉት ስምንት ቀናት “ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ምንድን ነው?” የሚለውን በዶርም ውስጥ አብረዋቸው ከነበሩት ኢትዮጵያውያን እህቶቻቸው መረዳታቸውን ገልጸዋል። “አንድ ላይ መሆን ምን ያህል እንደሚያምርብንና መለያየታችንን ያመጣው ያለን ልዩነት ሳይሆን ልብ ለልብ መራራቃችን መሆኑን ድምዳሜ ላይ አድርሶኛል” ብለዋል።
የሀገራዊ ምክክሩ ዋነኛ ዓላማ አካታች የሆነ የዜጎች ውይይት ማድረግ ነው፡፡ በተለይም ከዚህ ቀደም ትኩረት ያልተሰጣቸውና የጉዳት ሰለባ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ማካተት ዋነኛ ዓላማው አድርጎ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ ይህ ምክክር በርካታ ቁጥር ያላቸውን አካል ጉዳተኞች ያሳተፈ ምቹ ምህዳር የፈጠረ መሆኑን ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አካል ጉዳተኞችን ወክለው የመጡት ወ/ሮ ኮከቤ እንግዳሰውና አቶ ደረጄ ታደሰ ገልጸዋል። በሀገር ላይ በሚኖሩ አለመግባባቶችና ግጭቶች ዋነኛ ገፈት ቀማሽ አካል ጉዳተኛው በመሆኑ ሰላምን ቀዳሚ አጀንዳ አድርገው መሳተፋቸውን ገልጸዋል ።
ከ30 እስከ 35 ቀናት በሚቆየው የምክክር ሂደት አጀንዳዎቹ ለተከፋፈሉት ስምንት ቡድኖች ተሰጥተው ውይይት ይደረግባቸዋል፤ “ከዚህ ምክክር ምን ትጠብቃላችሁ?” ሲል መናኸሪያ ሬዲዮ ለተሳታፊዎች ጥያቄ አቅርቧል፡፡
ከኦሮሚያ ክልል የሴቶች ተወካይ ወ/ሮ አበበች አበራ፤ ሴቶች በዘመናት በነበሩ ግጭቶች ቀዳሚ ገፈት ቀማሽ በመሆናቸው፣ ባልን በማጣት፣ ልጅን በመቅበር እንዲሁም በራሳቸውና በሕፃናት ልጆቻቸው ላይ የሚደርሰውን አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ጥቃት ከግምት ውስጥ በማስገባትና በአሁኑ ወቅት ያለውን አናሳ የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሻሻል የሚያስችሉ ማሻሻያዎች ተደርገው በሕገ-መንግሥቱ ተገቢውን ቦታ የምናገኝበት ይሆናል ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።
“እኛ ተሳታፊዎች ታሪካዊ አደራ ከመላው ኢትዮጵያዊ የተረከብን ባለአደራዎች እንደመሆናችን፣ ከክልሌ ባለፈ ለሀገራዊ አንድነት የሚበጁ ሐሳቦችን አዋጥቼና ተቀብዬ ለመሄድ ነው የመጣሁት” ያሉት ደግሞ የሐረሪ ክልል የአስፈጻሚ አካል ተወካይ ወ/ሮ ኢማም መሐመድ ናቸው ።
“አካል ጉዳተኛው ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ዋጋ የከፈለና የተገለለ በመሆኑ፣ እንደ አንድ የአካል ጉዳተኛ ተወካይ ባለፉት የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቶች ስንጠይቅ የነበረው የአካታችነትና የመዋቅር ችግር መፍትሔ ያገኛል የሚል ትልቅ ግምት አለኝ” ሲሉ ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የመጡት ወ/ሮ ኮከቤ እንግዳሰው ተናግረዋል።
በዚህ ታሪካዊ የምክክር ሂደት ላይ ከአራቱም አቅጣጫ የተሰበሰቡ ኢትዮጵያውያን፣ የዲያስፖራው ማኅበረሰብ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአፍሪካ ኅብረት ተወካይ፣ የኢጋድ ዋና ጸሐፊና ሌሎችም ታድመዋል፡፡
በምክክሩ መክፈቻ ላይ የተገኙት የአፍሪካ ኅብረት ተወካይ አምባሳደር ባንኮሌ አዲዮይ “የኢትዮጵያ ሰላም መሆን የአህጉሩ ሰላም መሆን ነው” ብለዋል። ኢትዮጵያውያን ለሰላም ያላቸውን ተሳትፎ አድንቀው፣ እንደ አፍሪካ ኅብረት በቀጣይ ከምክክሩ የሚገኙ ውጤቶች ከአጀንዳ 2063 ጋር እንዲጣጣሙና የኢትዮጵያ የሰላም ጥያቄ እንዲመለስ ከጎናቸው እንደሚቆሙ ገልጸዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አረዓያ በመክፈቻው ባደረጉት ንግግር፤ በዚህ ታሪካዊ ሂደት ዋነኛ አካል በመሆናቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ ሀገራዊ መግባባት ስንጋጭባቸው የኖርናቸውን ችግሮች የሚቀርፍ መፍትሔ በተለያዩ አደረጃጀቶች መካከል ጠንካራ አዲስ እምነት እንዲገነባ የሚያደርግና ከሁሉ በላይ ደግሞ የውይይት ባህላችን ከዚህ በኋላም እንዲቀጥል ማስቻል ከዚህ ሀገራዊ ምክክር የሚጠበቁ ውጤቶች መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው፤ ይህ ውይይት “እኔነት” ተንጸባርቆበት የሚወጣበት ጉባኤ ሳይሆን “እኛ” የሚሉ ድምፆች የሚሰሙበት፣ በጋራ የመፍትሔ አካል መሆንን ያነገበ፣ አንዱ ለአንዱ ቁስል ምክንያት ሳይሆን የመዳን አቅም የሚሆንበት መሆን አለበት ብለዋል፡፡ በምክክሩ የሚነሱ ነጥቦች ሀገራዊ መሆን የሚችሉት ሌሎችን ሳያከፉ በ“እኛ” ውስጥ ሲያልፉ ብቻ በመሆኑ ውይይቱ በዚህ መንፈስ እንዲደረግ አደራ ብለዋል።
ከአራት ዓመታት በፊት የተቋቋመው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ ውስጥ አወዛጋቢ ናቸው የተባሉ ጉዳዮችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችና በውጭ ሀገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን አጀንዳዎችን ሰብስቦ ስምንት የመወያያ አጀንዳዎችን ጨምቆ በማውጣት የምክክር ሂደቱን በይፋ አስጀምሯል፡፡
ግጭት ሀገርን ያፈርሳል፤ መቃቃርን ያባብሳል፤ ሰላም እንዳትመለስ አድርጎ ያሸሻታል። ሀገር በዘላቂነት ሰላም የምትዘልቀው፣ ማኅበራዊ ቁርኝት የሚጠናከረውና ሀገራዊ መግባባት የሚፈጠረው ችግሮችን በውይይት በመፍታት መሆኑ ታምኖ ኢትዮጵያ መምከር ጀምራለች፡፡
ምላሽ ይስጡ