ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ም/ቤት ቋሚ መቀመጫ ለማግኘት በምታደርገው እንቅስቃሴ በኩል ተጠቃሚ ለመሆን በርካታ የዲፕሎማሲ ስራዎች ይጠበቁባታል ሲሉ ለመናኸሪያ ሬዲዮ የገለጹት የአለም አቀፍ ጉዳዮች ተመራማሪ አቶ እያሱ ኃ/ሚካኤል ናቸው፡፡
ተመድ የራሱ አሰራርና ህጎች የተቀመጡለት በመሆኑ አባል ለመሆን ኢትዮጵያ በምታደርገው ጥረት ውስጥ አባል የሆኑት ሃገራት በሚያደርጉት የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ተናግሮ ከማሳመን ጀምሮ ፋይናንስ በመመደብ ህግና ደንቡን ተከትላ የምትሰራ መሆን ይጠበቅባታል ፤ ይህም ከሃገራቱ ጋር ከፍተኛ ፉክክርና ውድድር የሚጠይቅ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በዋናነት ሃገሪቷ በምታሳየው የጸጥታና የመረጋጋት ሁኔታና እንዲሁም በአለማቀፍ ጉዳዮች የሚኖራት ንቁ ተሳትፎና ሚና መሰረት በማድረግ በመሆኑ ኢትዮጵያ የሚጠበቁባትን ሂደቶች በመተግበር ዝግጁ ሆና መጠበቅ ይገባታል የሚሉት ተመራማሪው ፤ በተጨማሪም የተለያዩ የኢኮኖሚ ማእቀፎችንና ማህበራትን ማጠናከር ብሎም በአፍሪካ ጉዳዮች ውስጥ ጠንከር ያለ የሰላም ማስከበርና ቀጠናዊ ትሥሥርን ማስተግበር እንደሚገባትም አመላክተዋል ።
ሌላኛው የአለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አቶ አበራ ሂጲሶ፤ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ም/ቤት ቋሚ መቀመጫ ለማግኘት በርካታ የዲፕሎማሲ ስራዎችን በመስራትና አሁን ላይም የጀመረቻቸውን የዲፕሎማሲ አካሄዶች አጠናክራ መቀጠል እንደሚገባት ገልጸዋል፡፡ ጥያቄ ምላሽ ቢያገኝ የአለም ትኩረትን ለመሳብና ለአፍሪካም እንደ አንድ መልክ ሊታይ የሚያስችል ነው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ደርጅት የጸጥታው ም/ቤት ቋሚ መቀመጫ ለማግኘት የጀመረችውን ጉዞ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድን በተከተለ መልኩ ማጠናከር እንዳለባት ተመላክቷል፡፡
ምላሽ ይስጡ