ግንቦት 05 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ለ2018 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ተፈታኞች የመፈተኛ ክፍል መግቢያ ካርድ (Admission Card) መለቀቁን አስታውቋል።
ከመጪው ሰኔ 24 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሚሰጠው ፈተና የተዘጋጀው ይህ ካርድ ከግንቦት 03 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በፈተና አስተዳደር ሲስተም በኩል ለክልል ትምህርት ቢሮዎች፣ ለዞን ትምህርት መምሪያዎች እና ለትምህርት ቤት ተወካዮች ተለቋል።
በመመሪያው መሰረት እያንዳንዱ ተፈታኝ ተማሪ በአድሚሽን ካርዱ ጀርባ ላይ የትምህርት ቤቱ ወይም የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ማህተም ያረፈበትን ኦሪጅናል ካርድ ከትምህርት ቤቱ ወስዶ በእጁ መያዝ ይኖርበታል።
በተጨማሪም በምዝገባ ወቅት የተከሰቱ የትምህርት መስክ፣ የጾታ፣ የፎቶ እና መሰል የመረጃ ግድፈቶች ካሉ ተፈታኞች እስከ ግንቦት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ለትምህርት ቤታቸው በማሳወቅ ሂደቱን ጠብቀው እንዲያስተካክሉ ተሳስቧል።
አድሚሽን ካርዱ ወደ መፈተኛ ማዕከልም ሆነ ክፍል ለመግባት ብቸኛው መታወቂያ በመሆኑ ተፈታኞች ካርዳቸውን በአግባቡና በጥንቃቄ መያዝ እንዳለባቸው አገልግሎቱ ገልጿል።
ከዚህም ባሻገር ተፈታኞች በፈተና ወቅት ከካርዱ በተጨማሪ የፋይዳ (ብሄራዊ) መታወቂያ መያዝ ግዴታቸው መሆኑ ተመላክቷል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ