ግንቦት 06 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ፤ የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ተቋም ዳይሬክተር ጉብኝት ኢትዮጵያ ለጀመረችው ሰፊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲሁም ለሀገሪቱ ጠቅላላ ኢኮኖሚ የሚኖረው አስተዋጽኦ በበጎ የሚታይ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህም ባሻገር ጉብኝቱ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍ የሚረዱ የፋይናንስ ድጋፎች እንዲመቻቹ መንገድ የሚጠርግ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ የሀገሪቱን የዕዳ ጫና ለማቃለል ከሚደረገው ድርድር ጋር ቀጥተኛ ትስስር እንደሚኖረው አመልክተዋል። የዓለም አቀፍ ተቋማት እና ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላቸው ሀገራት መሪዎች መምጣታቸው ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በጎ አስተዋጽኦ እንዳለውም አክለዋል።
በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ አቶ አበራ ሄጲሶ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የሚደረጉ የኃያላን ሀገራት እና የግዙፍ ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ጉብኝት ከሀገሪቱ ተፅዕኖ ፈጣሪነት አንጻር የሚታዩ መሆናቸውን ተናግረዋል። የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ እንዲሁም የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ዳይሬክተር በአዲስ አበባ መገኘት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ተፅዕኖ ፈጣሪነት መሰረት ያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
የመሪዎቹ ጉብኝት በምዕራባውያን እና በአዳጊ ሀገራት መካከል ባለው የኃይል ሚዛን ውስጥ የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ተፈላጊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን ያመላክታል ብለዋል። በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ በታላላቅ ኃይሎች መካከል ያለውን ፍላጎት በማመጣጠን ሉዓላዊነቷን እና ብሔራዊ ጥቅሟን እያጠናከረች እንድትወጣ የሚያስችላትን የዲፕሎማሲያዊ አካሄድ መከተል እንደሚገባትም አስገንዝበዋል።
በዘንድሮ ዓመት ኢትዮጵያ ካስተናገደቻቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች በተጨማሪ በርካታ የአውሮፓ፣ የእስያ እና የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ያደረጉት ጉብኝት ሀገሪቱ ያላትን ተሰሚነት የሚያሳድግ በመሆኑ፣ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር መጠቀም እንደሚገባ ተጠቁሟል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ