ግንቦት 05 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የ6 ዓመት ህፃን በማገት እና ቤተሰቦቹን ለገንዘብ በመደራደር ወንጀል የተከሰሱ ሁለት ግለሰቦች በ12 እና በ9 ዓመት ጽኑ እስራት መቀጣታቸውን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ አስታወቀ።
እንደ ፖሊስ መዝገብ መረጃ፣ አንደኛ ተከሳሽ እንዳሻው በቀለ እና ሁለተኛ ተከሳሽ ጌቱ ገረመው የተባሉ ግለሰቦች ብሩክ ወልደኪዳን የተባለውን ህፃን ከዲላ ከተማ አግተው ወደ ሲዳማ ክልል በመውሰድ ደብቀውት ቆይተዋል።
ተከሳሾቹ ህፃኑን ለመልቀቅ ከቤተሰቦቹ ጋር በገንዘብ ሲደራደሩ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ ፖሊስ ከአጋር የፀጥታ አካላትና ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ባደረገው ተከታታይ ክትትል አጋቾቹን በቁጥጥር ስር አውሎ ህፃኑን በሰላም ለወላጆቹ ማስረከብ ችሏል።
የዲላ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአቃቤ ህግን የምርመራ መዝገብና የቀረበውን ክስ መርምሮ፣ ተከሳሾቹ በፈጸሙት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው አንደኛው በ12 ዓመት፣ ሁለተኛው ደግሞ በ9 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል።
የክልሉ ፖሊስ መሰል ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን ለመከላከል ከህብረተሰቡ ጋር ያለውን ቅንጅት አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ፣ ወላጆች ለልጆቻቸው ደህንነት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉና አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲገጥሟቸው ለፀጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጡ አሳስቧል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ