ነሐሴ 26 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የ2019 አዲስ ዓመት በዓልን ምክንያት በማድረግ የሚፈጠረውን የኅብረተሰቡን ከፍተኛ መሠረታዊ ፍጆታ ምርቶች ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል ሰፊ የዝግጅት፣ የአቅርቦትና የቁጥጥር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። ለበዓሉ ገበያ ከቀረቡትና ለማቅረብ ከታቀዱት ዋና ዋና የግብርና ምርቶች መካከል 700 ሺሕ 8 ሺሕ 266 (708 ሺሕ 266) ኩንታል ቀይ ሽንኩርት፣ ከ1 ሚሊዮን 11 ሺሕ ኩንታል በላይ አትክልትና ፍራፍሬ፣ 227 ሺሕ 885 ኩንታል የጤፍ ምርት፣ 125 ሺሕ 321 ኩንታል ስንዴና ገብስ፣ እንዲሁም ከ79 ሺሕ ኩንታል በላይ የስንዴ ዱቄት እና ከ3.7 ሚሊዮን ሊትር በላይ ፈሳሽ የምግብ ዘይት ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ ዝግጅት መጠናቀቁን የቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ ተናግረዋል። የቄራ እንስሳት አቅርቦትን በተመለከተም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዶሮዎች፣ ከ42.7 ሚሊዮን በላይ እንቁላል፣ ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ በግና ፍየል እንዲሁም 62 ሺሕ 600 ደረቅ ከብቶች ለበዓሉ ገበያ እንደሚቀርቡ ገልጸዋል። ምርቶቹን ለኅብረተሰቡ በጥራትና በበቂ ሁኔታ ለማዳረስ ሲባል 7 የሰብል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የፋብሪካ ምርቶች መሸጫ ማዕከላት፣ 5 የቀንድ እንስሳት መሸጫ ማዕከላት እና 264 የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ሳምንቱን ሙሉ ክፍት ሆነው አገልግሎት እንዲሰጡ መወሰኑን ኃላፊዋ ጠቁመዋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ