ሰኔ 10 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) በአፍሪካ የሲቪል ማኅበራት ኅብረት (ሲሲአርዲኤ) ከውጭ በሚገኝ ዕርዳታ ላይ ከመጠን በላይ ጥገኝ መሆን ሀገራዊ የቤት ሥራዎችን በአግባቡ እንዳይሠሩ እያደረገ መሆኑን ገለጸ።
በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል እየተካሄደ በሚገኘውና ከ30 በላይ አገራት የተውጣጡ ከ600 በላይ ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ባሉበት 10ኛው የምስራቅ አፍሪካ የበጎ አድራጎት ጉባኤ (East Africa Philanthropy Conference) ላይ በጎንዮሽ መግለጫ የሰጡት የኅብረቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሥ ለገሰ፣ የአፍሪካ አገራት የራሳቸውን የውስጥ አቅም ማጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ የወቅቱን ዓለም አቀፍ ሁኔታና ሊወሰድ የሚገባውን መፍትሔ ሲያብራሩ “የውጭ ድጋፎች እንደ ዱሮው በማይቀጥሉበት በአሁኑ ወቅት፣ አፍሪካውያን በራስ የመረዳዳትና የሀገር ውስጥ ሀብትን የማሰባሰብ ባህልን ሊያሳድጉ ይገባል” ያሉ ሲሆን፣ አፍሪካውያን የሀገር ውስጥ ሀብትን በማስተባበር ረገድ ከኢትዮጵያ ትልቅ ተሞክሮ መውሰድ እንደሚችሉ ሲጠቅሱም “የኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ፣ ሕዝብንና ሀብትን በማስተባበር ያለ ምንም የውጭ ሳንቲም ሜጋ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደሚቻል ትልቅ ማረጋገጫ ነው፤ አፍሪካውያንም ከዚህ በመማር በራሳቸው ሪሶርስ ራሳቸውን ማቋቋም አለባቸው” ሲሉ አሳስበዋል።

ከሰኔ 9 እስከ ሰኔ 13 ቀን 2018 ዓ.ም (እ.ኤ.አ. ከሰኔ 16 እስከ 20 ቀን 2026) በሚቆየው በዚህ ታላቅ ጉባኤ ላይ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መሪዎች፣ የግል ዘርፍ ተወካዮች፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሲቪል ማኅበራት መሪዎች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ባለሀብቶች፣ የዲያስፖራ በጎ አድራጊዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የሚዲያ ባለሙያዎች እንዲሁም ቀጣዩን ኃላፊነት ለመረከብ የሚዘጋጁ ወጣት መሪዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
የዘንድሮው ጉባኤ “የሽግግር ሥርዓቶችን በአስተማማኝ መሠረት ላይ መገንባት” (Anchoring Systems in an Era of Transition) በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ሲሆን፣ በዘርፉ ላይ ያለውን አመኔታና ተዓማኒነት መልሶ ለመገንባት የሚያስችሉ የአሠራር ለውጦች (operational transformation) ዙሪያ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
ይህ ዓመታዊ ጉባኤ በየዓመቱ በበጎ አድራጎት ዘርፍ ውስጥ የሚነሱ አንጋፋ ተግዳሮቶችን፣ ወቅታዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን እና አፋጣኝ ምላሽ የሚሹ አዳዲስ ክስተቶችን በጋራ ለመገምገም የሚካሄድ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ መድረክ ሲሆን፣ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመለየት፣ የተቋማት ትስስር ለመፍጠር እና ዘርፉ በቀጠናው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሽግግሮች ውስጥ ያለውን ሚና ለማጠናከር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተመልክቷል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ