ሰኔ 23 ቀን 2017 (መናኸሪያ ሬዲዮ)በኢትዮጵያ የረጅም ርቀት አሽከርካሪዎች እየደረሰባቸው ካለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ባለፈ ጠረፍ አካባቢ ያለው ከፍተኛ የሙቀት መጠን ለህልፈት እየዳረጋቸው መሆኑን የኢትዮጵያ የከባድ ተሽከርካሪ አሽከርካሪዎች ማህበር ገልጿል።
የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ዘውዴ፤ በዘርፉ የተሰማሩ ዜጎች በሙቀት እና ተያያዥ ምክንያቶች ለህልፈት እየተዳረጉ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ከሰሞኑን 3 የማህበሩ አባላት በጅቡቲ በነበረው ከባድ ሙቀት ህይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል።
ማህበሩ በቻለው መጠን ለህልፈት የተዳረጉ አሽከርካሪዎችን አስክሬን በማንሳት ለቤተሰቦቻቸው ማድረስ እንደቻለም አመላክተዋል፡፡
ሆኖም አስክሬኑን ለማንሳት እና ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት እየተጠየቀ ያለው ገንዘብ ከፍተኛ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡
የሚጠየቀውን ገንዘብ እና የቆይታ ጊዜ መጠን ለመቀነስ ማህበሩ ጥረት እያደረገ ቢሆንም ሙቀቱ ተፈጥሯዊ በመሆኑ እና እስከ ቀጣዮቹ ወራት ድረስ የሚዘልቅ በመሆኑ አሳሳቢ አድርጎቷል ይላሉ፡፡
በአገልግሎት አሰጣጥ ወቅት ወረፋ የሚበዛበት አሰራር አለመዘመኑ አሽከርካሪዎች ስራቸውን በአግባቡ ማከናወን እንዳይችሉ፤ የቆይታ ጊዜያቸውም እንዲራዘም ብሎም ህይወታቸው እንዲያልፍ እያደረጋቸው ነው ሲሉ አክለዋል።
የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ ከሰሞኑን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ፣ በጅቡቲ የወደብ አገልግሎት በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ እየተስተዋለ ያለው ችግር በርካታ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ በጅቡቲ ወደብ በአገልግሎት አሰጣጥ ሒደት በሚኖር ቆይታ፣ እያስወጣ ያለው ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ አማራጭ አሰራሮችን መጠቀም ይገባል ብለዋል። በድሬዳዋ ያለውን ነጻ የንግድ ቀጠና እና የሞጆ ደረቅ ወደብን መጠቀም በአንጻሩ ያሉ ችግሮችን የሚፈታ አማራጭ እንደሚሆን ጠቅሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ የረጅም ርቀት አሽከርካሪዎች በርካታ ችግሮች እያጋጠማቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
Telegram 👉 https://t.me/menaharia_fm
ምላሽ ይስጡ