የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ማስታወሻ አዲሱ የጉዞ እገዳ እቅድ አፍሪካ፣ ካሪቢያን፣ መካከለኛው እስያ እና የፓሲፊክ አገራትን ያነጣጠረ መሆኑ ተገልጿል።
በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሚመራው አስተዳደር የጉዞ ክልከላውን በከፍተኛ ደረጃ እያስፋፋ መሆኑ እየተገለጸ ሲሆን፣
ከሰሞኑን ደግሞ ከ36 ተጨማሪ ሀገራት ወደ አሜሪካ መግባትን የሚገድብ ሚስጥራዊ ሰነድ መዘጋጀቱን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስታወሻ አሳይቷል ሲል አናዶሉ ዘግቧል።
በዋሽንግተን ፖስት የተገኘው ማስታወሻው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የተፈረመ እና ቅዳሜ የተፃፈ ሲሆን ኢላማ የተደረገባቸው ሀገራት የአሜሪካን መመዘኛዎች እንዲያሟሉ የ60 ቀናት ቀነ ገደብ እንደተቀመጠላቸው ይገልፃል።
አገራቱ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የቪዛ ክልከላ ይጠብቃቸዋል ተብሏል።
ዝርዝሩ እንደ ግብጽ፣ ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ያሉ ቁልፍ የአሜሪካ አጋሮችን እንደሚያጠቃልል እና 25 የአፍሪካ ሀገራት እንዳሉበት ታውቋል።
ከመካከለኛው እስያ፣ ከካሪቢያን እና ከፓስፊክ ውቅያኖስ በርካታ አገራትም አሉበት።
በሰነዱ መሰረት፣ የጉዞ እገዳው የሚጠብቃቸው አገራት አስተማማኝ የመታወቂያ ሰነዶችን የማያሟሉ፣ በሲቪል መዝገብ ውስጥ ሰፊ ማጭበርበር የታየባቸው፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የቪዛ ቆይታ ያላቸው፣ የመኖሪያ ፍቃድ ሳይኖራቸው በኢንቨስትመንት የዜግነት መብት ማገኘት እና “በአገሪቱ ፀረ-ሴማዊ እና ፀረ-አሜሪካዊ ድርጊት ይፈጽማሉ የተባሉት መሆናቸው ተመላክቷል።
የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በጉዳዮ ዙሪያ አስተያየት ከመስጠት መቆጠቡን ዘገባው ጠቅሷል።
የዴሞክራቶች እና የሲቪል መብት ተሟጋቾች እቅዱን በፍጥነት አውግዘዋል። ተቺዎቹ ውሳኔውን የአፍሪካ እና የካሪቢያን ሃገራት ላይ ኢላማ ያደረገ አድሎአዊ ሲሉም ተቃውመውታል።
ምላሽ ይስጡ