ጥቅምት 26 ቀን 2019(መናኸሪያ ሬዲዮ) በአሁኑ ወቅት ፈጣን የኢንፎርሜሽን እና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዕድገት በሁሉም የግንኙነት ዘርፎች ውስጥ እየጨመረ በመምጣቱ አገልግሎቶችና የንግድ ግብይቶች በዲጂታል የግብይት መረብ ሥርዓት ማዕቀፍ ውስጥ እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በዚህ ሂደት ውስጥም የተሳታፊዎችን ማንነት እና የመልዕክቶችን ትክክለኛነት በማረጋገጥ መተማመን ለመፍጠር የሚያስችል ሁኔታ እንዲኖር ይደረጋል።
ይህንን ለማድረግ ከሚያስችሉ ቁልፍ ሐሳቦች መካከል ፊርማ አንዱ ሲሆን፤ ፊርማውም ከቴክኖሎጂው ጋር የሚጣጣም እንዲሆን በአዋጅ ቁጥር 1072/2010 እና በማሻሻያው አዋጅ ቁጥር 1358/2017 ሕጋዊ እውቅና አግኝቷል።
የኤሌክትሮኒክ ፊርማ ማለት ከኤሌክትሮኒክ መልዕክት ጋር በተያያዘ ፈራሚውን ለመለየትና በመልዕክቱ የተካተተው መረጃ በፈራሚው የፀደቀ ወይም ተቀባይነት ያገኘ መሆኑን ለማመልከት ጥቅም ላይ የሚውል፣ በኤሌክትሮኒክ መልዕክት ላይ የተለጠፈ ወይም ከመልዕክቱ ጋር ምክንያታዊ በሆነ አኳኋን የተቆራኘ መረጃ ነው።
በሌላ በኩል ዲጂታል ፊርማ ማለት አሴሜትሪክ ክሪፕቶ ሥርዓትን የሚጠቀም፣ ከፈራሚው ጋር በልዩ ሁኔታ የተቆራኘ፣ የፈራሚውን ማንነት መለየት የሚያስችል እና በፈራሚው ሙሉ ቁጥጥር ሥር ብቻ ባለ ምስጢራዊ ቁልፍ የተፈጠረ የኤሌክትሮኒክ ፊርማ ዓይነት ነው።
ማንኛውም የኤሌክትሮኒክ መልዕክት እና የኤሌክትሮኒክ ፊርማ ሕጋዊ ተቀባይነትና ተፈጻሚነት አለው። በፍትሐብሔር ፍርድ ሂደት የቀረበ አስተማማኝ የኤሌክትሮኒክስ ፊርማ በተቃራኒ ማስረጃ እስካልተስተባበለ ድረስ የባለቤቱ ፊርማ እንደሆነ፣ ፈራሚው እያወቀ የፈረመበት መሆኑን እና ፊርማው ካረፈበት ጊዜ አንስቶ እንዳልተቀየረ የሕግ ግምት ይወሰዳል።
በጸና ሰርተፍኬት የተደገፈ ዲጂታል ፊርማም አስተማማኝ የኤሌክትሮኒክ ፊርማ ተብሎ ይገመታል።
የሩት ሰርተፊኬት ባለሥልጣን የተሰጠ የጸና ፈቃድ ሳይኖረው በሰርተፊኬት ሰጪነት አገልግሎት መሰማራት የተከለከለ ነው። ፈቃድ የተሰጣቸው አካላት ለተገልጋዮች ዋስትና የመስጠት፣ የሰርተፊኬቱን አገልግሎት ሁኔታዎች በግልጽ የማሳወቅ እና ክፍያዎችን የማስጸደቅ ኃላፊነት አለባቸው።
ፈቃድን አላግባብ መጠቀም ወይም ሕግን መተላለፍ በሕግ ያስቀጣል።
ተገልጋዮች ትክክለኛ እና የተሟላ መረጃ የመስጠት፣ ምስጢራዊ ቁልፋቸው ለአደጋ እንዳይጋለጥ የጥንቃቄ እርምጃዎችን የመውሰድ እና ጉዳዩን የማሳወቅ ግዴታ አለባቸው ተብሏል።
በሌላ በኩል በሰርተፊኬት ላይ እምነት የሚያሳድሩ አካላት የማረጋገጫ መንገዶችን የመከተል፣ የተሰጡ የመተማመኛ ገደቦችን የማክበር እና የሰርተፊኬቱን ወቅታዊ ሁኔታ የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለባቸው በፍትህ ሚኒስቴር በንቃተ ሕግ እና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ ጹሁፍ ላይ ተመላክቷል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ