ጥቅምት 25 ቀን 2019(መናኸሪያ ሬዲዮ) በጠፈር ጥልቀት ውስጥ ሳይንቲስቶችን ያስደመመ አንድ አስደናቂ ክስተት ተከስቷል። RBH-1 ተብሎ የተሰየመውና ከራሱ ጋላክሲ ተገፍትሮ የወጣው ግዙፉ ጥቁር ቀዳዳ (Supermassive Black Hole)፣ በሰከንድ 954 ኪሎ ሜትር በሚደርስ አስገራሚ ፍጥነት የጠፈርን ባዶነት እየሰነጠቀ ይጓዛል።
በተለምዶ ጥቁር ቀዳዳ ሲባል በአቅራቢያው ያለውን ማንኛውንም ነገር ውጦ የሚያጠፋ አስፈሪ አካል እንደሆነ እናስባለን። የዚህኛው ጉዞ ግን የተለየ ነው፤ ይሄኛው ጥቁር ቀዳዳ በጥፋት ፈንታ ከኋላው የ200,000 የብርሃን ዓመታት ርዝመት ያለው የአዲስ ሰማያዊ ኮከቦች ማህፀን እያስከተለ ይገኛል። በከፍተኛ ፍጥነት እየተጓዘ ከፊቱ ያለውን የጋዝ ደመና ሲገፋውና ሲጋፈጠው፣ ደመናው ተጨመቆ ለአዳዲስ ኮከቦች መወለድ ምቹ ሁኔታ ተፈጠረ።
ይህ አካል የሚጓዝበት ፍጥነት በሰዓት ከ3.4 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር በላይ ሲሆን፣ በዚሁ ፍጥነቱ ከተጓዘ በመሬትና በጨረቃ መካከል ያለውን ርቀት ከ7 ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ አቋርጦ ማጠናቀቅ ይችላል ነው የተባለው።
ለመሆኑ ይሄን ያህል ግዙፍ አካል ከራሱ ጋላክሲ ያስወጣው ምን ይሆን? ተመራማሪዎች እንደሚገምቱት ከሆነ፣ ከብዙ ሚሊዮን ዓመታት በፊት በሁለት ወይም በሦስት ግዙፍ ጥቁር ቀዳዳዎች መካከል በተፈጠረ ኃይለኛ የስበት ትግልና ውህደት ምክንያት እንደ ኳስ ተገፍትሮ ወደ ውጪ ሊወጣ ችሏል።
ይህ ግኝት ጥቁር ቀዳዳዎች ቁሳቁሶችን የሚያወድሙ ብቻ ሳይሆኑ፣ ለአዳዲስ ኮከቦችና ጋላክሲዎች መፈጠር መንገድ የሚከፍቱ የጠፈር ፈጣሪዎችም ሊሆኑ እንደሚችሉ አዲስ እይታን ፈጥሯል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ