ሕዳር 15 ቀን 2019(መናኸሪያ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የሚገኙ አብዛኞቹ ወጣቶች ከበሽታ መከላከል ይልቅ እርግዝና ብቻ እያስፈራቸው መምጣቱን “ኤድስ ሄልዝ ኬር ፋውንዴሽን” በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው 5ኛው የአፍሪካ የሕብረተሰብ ጤና ጉባኤ ጎን ለጎን ባካሄደው መድረክ ላይ አስታውቋል።
ወጣቶች ኮንዶም ከመጠቀም ይልቅ የድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ እንክብሎችን (ፖስት ፒል) መጠቀምን እየመረጡ መምጣታቸው እጅግ አስጊ መሆኑን የፋውንዴሽኑ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቶለሳ ኦላና ተናግረዋል። በድርጅቱ አዲስ የጥናት ግኝት መሠረት በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጣቶች ኮንዶም መጠቀምን እየተዉ ወደ ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ እንክብሎች ማዘንበላቸው ለኤች.አይ.ቪ (HIV) እና ለሌሎች በግብረ ሥጋ ግንኙነት ለሚተላለፉ በሽታዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ እንደሚያደርጋቸው ተገልጿል።

ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከል ተገቢ ቢሆንም እንደ ጥናቱ ግኝት ከሆነ፣ ወጣቶች በግንኙነት ወቅት ዋነኛ ትኩረት የሚሰጡት ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል ብቻ መሆኑ ኮንዶም የመጠቀም ልማድን በመቀነስ ወጣቶች ለበሽታ ስርጭት ግዴለሽ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
በወጣቶች ዘንድ የሚስተዋለውን ይህንን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላት እና የኮንዶም አጠቃቀም ባህልን መልሶ ለማሳደግ የጤና ተቋማትና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሠሩ ጥሪ ያቀረበው “ኤድስ ሄልዝ ኬር ፋውንዴሽን”፣ የድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ እንክብሎች እርግዝናን ከመከላከል ባለፈ ከኤች.አይ.ቪም ሆነ ከማንኛውም የአባለዘር በሽታ እንደማይከላከሉ ወጣቶች በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው እንደሚገባ አቶ ቶለሳ አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ