ራሚስ ባንክ 2 ሚሊዮን 101 ሺህ 106 አክሲዮኖችን በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን በይፋ ማስመዝገቡንና በኢትዮጵያ ሰነዶች ማኅበራዊ ገበያ (ESX) ዋና ሰሌዳ ላይ ለመመዝገብ ላቀረበው ማመልከቻ በመርህ ደረጃ ፈቃድ ማግኘቱን አስታውቋል።
ሁለቱ ስኬቶች በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ውስጥ ለባንኩ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍቱ መሆናቸው ተገልጿል።
የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሊ አህመድ እንደገለጹት፤ በካፒታል ገበያ ባለሥልጣኑ የተሰጠው የአክሲዮኖች ምዝገባ ማጽደቂያ እና በዋና ሰሌዳው ላይ ለመመዝገብ የተሰጠው የመርህ ደረጃ ፈቃድ የባንኩን ተቋማዊ አቅም፣ የኮርፖሬት አስተዳደር ሂደትና የተዓማኒነት አቅም የሚያሳይ ስኬት ነው።
የነባር ባለአክሲዮኖችን አክሲዮን በይፋዊ ገበያ ላይ ለመሸጥና ለማስተላለፍ የሚያስችለው ሂደት የሀብት እሴትን ከማሳደግ ባለፈ ፈጣን የገንዘብ ዝውውርን እንደሚያበረታታ አቶ አሊ ገልጸዋል። በቀጣይም የአክሲዮን አስተዳደር ሥርዓቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል ለማሸጋገርና የግብይት ሂደቱን ለማቀላጠፍ እንደሚሠራ አመልክተዋል።

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ራቢ ሼክ ሁሴን በበኩላቸው፤ ባንኩ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በሸሪዓ መርሆች፣ በግልጽነትና በጠንካራ ተቋማዊ አስተዳደር ላይ በመመሥረት የሕብረተሰቡን እምነት ማግኘት መቻሉን ገልጸዋል። ባንኩ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ሪፎርም በመጠቀም በምሥራቅ አፍሪካ የወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ዋና ማዕከል የመሆን ራዕዩን ለማሳካት በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በዚህም ራሚስ ባንክ በኢትዮጵያ ሰነዶች ማኅበራዊ ገበያ ዋና ሰሌዳ ላይ ለመመዝገብ በመርህ ደረጃ ፈቃድ ካገኙ የወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሃና ተለከቁ፣ ራሚስ ባንክ ወደዚህ ሥርዓት መግባቱ ለባንኩ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ለተዓማኒነት፣ በገበያው ላይ ቀጣይነት ላለው የኢኮኖሚ አስተዋፅዖ እንዲሁም ለሀገር የካፒታል እድገት ከፍተኛ አበርክቶ እንዳለው አመላክተዋል።
እንደነዚህ ያሉ መረጃ የማረጋገጥና ዕውቅና የመስጠት ሂደቶች ከፍተኛ ጥንቃቄና ትኩረት የሚፈልጉ በመሆናቸው ጊዜ እንደሚወስዱ ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል። ተቋማት ይህን በትዕግሥት ጠብቀው ተሳታፊ እንዲሆኑ የጠየቁ ሲሆን፣ ሌሎች ወደዚህ ሥርዓት ያልገቡ ባንኮችም በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ዕውቅና ለማግኘት የሚደረገውን ሂደት እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ምላሽ ይስጡ