ግንቦት 18 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የዒድ አል-አድሃ (ዓረፋ) በዓል ሲከበር በመረዳዳት እና በመተሳሰብ ሊሆን እንደሚገባ ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስተያየታቸውን የሰጡ የሃይማኖት አባቶች ገልጸዋል።
በሃይማኖታዊ ሥርዓቱ መሠረት ከሶላት መልስ የእርድ ሥነ-ሥርዓቱ እንደሚከናወንና ቢያንስ አንድ ሦስተኛውን ለተቸገሩ የማካፈል ሕግ መኖሩን በአዲስ አበባ የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የፈትዋ፣ የጥናትና ምርምር ዘርፍ አባል ኡስታዝ ሸምሰዲን ባሕሪ ለጣቢያችን ገልጸዋል።
የእስልምና ተከታይ ማኅበረሰቡ ይህንን ሥርዓት ለዘመናት ሲያከናውን መቆየቱንና አሁን ላይ ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሙዕሚኑ መረዳዳትን ሊያስቀጥል የሚገባው ዘመን ላይ ስለመሆናችን ኡስታዙ በአጽንኦት ተናግረዋል።
ለተቸገሩት ብቻ ሳይሆን ከጓደኛ፣ ከጎረቤትና ከወዳጅ ዘመድ ጋር ተጠራርቶ አብሮ በማክበር የአረፋ በዓል ሙዕሚኑን ይበልጥ ለማቀራረብ አጋዥ ክብረ በዓል መሆኑን በማስታወስ፣ ማኅበራዊነትን ማጠናከር እንደሚገባ ተገልጿል።
በሌሎቹም በዓላት ሁሉ መረዳዳት የሚመከርና ሕጉም የሚያዘው ቢሆንም፣ በተለይ በአረፋ በዓል ደግሞ ሕዝበ ሙስሊሙ ሃይማኖቱ የሚያዘውን ትእዛዝ በመፈጸም ሊረዳዳ እንደሚገባ ይመከራል ሲሉ ለጣቢያችን አስተያየታቸውን የሰጡት ኡስታዝ ካሚል ኃሚድ ተናግረዋል።
የአረፋ በዓል የሚከበርበትን ሃይማኖታዊ ምስጢር ተረድቶ መታዘዝንና ለተቸገሩ መድረስን ይበልጥ ሕዝበ ሙስሊሙ የሚያውቅበትና የሚተገብርበት እንደሆነም ኡስታዝ ካሚል ገልጸዋል።
1447ኛው የዒድ አል-አድሃ (ዓረፋ) በዓል ነገ ረቡዕ ግንቦት 19 ቀን ተከብሮ እንደሚውል መገለጹ ይታወቃል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ