መስከረም 04 ቀን 2019ዓ.ም.(መናኸሪያ ሬዲዮ) በዩክሬን እና በፖላንድ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው የያሆዲን የባቡር ጣቢያ ላይ የሩሲያ ድሮን ጥቃት ማድረሱ ተገለፀ። ጥቃቱ የተፈፀመው የቀድሞው የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን እና የቀድሞው የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር ካርል ቢልድትን ጨምሮ ከፍተኛ የአውሮፓ የደህንነት አማካሪዎች ጣቢያውን በባቡር ለቀው ከተጓዙ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ነው። በኪየቭ በተካሄደው የያልታ የአውሮፓ ስትራቴጂ ጉባኤ ላይ ተካፍለው ወደ ፖላንድ በመመለስ ላይ የነበሩት ዲፕሎማቶች የነበሩበት ባቡር አስቀድሞ በተደረገ የጊዜ ሰሌዳ ለውጥ ምክንያት ቀደም ብሎ ከጣቢያው በመውጣቱ ከጥቃቱ ማምለጡ ተጠቅሷል። የዩክሬን የባቡር መስመር አስተዳደር ባወጣው መግለጫ የሩሲያ ድሮን ዋና ዒላማ ዲፕሎማቶቹን የጫነው ባቡር ሊሆን እንደሚችል ያለውን ግምት አስታውቋል። በጥቃቱ ሳቢያ በጣቢያው በቆመው ሌላ የባቡር ሞተር (ሎኮሞቲቭ) ላይ ጉዳት የደረሰ ቢሆንም፣ ከተሳፋሪዎች መካከል በሰው ህይወትና አካል ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን እና የደህንነት ስርዓቱ በወቅቱ ሰዎችን ማ ስወጣቱ ተገልጻል። በጥቃቱ ወቅት የቀድሞው የሲአይኤ (CIA) ዳይሬክተር ዴቪድ ፔትሬየስ የተሳፈሩበት ሌላ ባቡር በጣቢያው እንደነበርና ተሳፋሪዎችም በአስቸኳይ መወጣታቸው ተመልክቷል። ስለ ድሮን ጥቃቱ አስተያየት የሰጡት ቦሪስ ጆንሰን ድርጊቱን በሲቪል የባቡር መስመሮች ላይ የተፈፀመ ምክንያታዊ ያልሆነ ጥቃት ሲሉ የኮነኑት ሲሆን፣ የዩክሬን ወገንም ጥቃቱን የሀገሪቱን የመጓጓዣ መሰረተ ልማቶች ለማስተጓጎል እና ፍርሃት ለመፍጠር የተደረገ እንቅስቃሴ ነው ብሎታል። በሌላ በኩል የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ በምዕራብ ዩክሬን በሚገኙ የባቡር መሰረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ማድረሱን አረጋግጦ፣ እርምጃው ወታደራዊ ቁሳቁሶችን እና ጭነቶችን የሚያጓጉዙ ስትራቴጂካዊ ቦታዎችን ኢላማ ያደረገ እንደሆነ አስታውቋል።
___
ሀሳብ እና‘ሳ‘ፍራለን
ምላሽ ይስጡ