ነሐሴ 22 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የስሜን ኮሪያ መንግሥት በዜጎቹ የስልክ አጠቃቀም ላይ የሚያደርገውን የሳይበር ቁጥጥር እና የዲጂታል ሳንሱር እጅግ ማጠናከሩን የደህንነት እና የቴክኖሎጂ ተመራማሪዎች ዘገባዎች ያመላክታሉ። በሀገሪቱ ውስጥ ባሉ ስማርትፎኖች ላይ በተጫነ ልዩ የሶፍትዌር ሥርዓት አማካኝነት ስልኮቹ የተጠቃሚውን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚያሳይ የስክሪን ምስል በዘፈቀደ እና በየጊዜው እንደሚያነሱ ተረጋግጧል። “ሬድ ስታር ኦኤስ” (Red Star OS) በተሰኘው የሀገሪቱ ማሻሻያ በተደረገበት የአንድሮይድ ሶፍትዌር ውስጥ Traceviewer የተባለ አብሮ የተሰራ የመከታተያ ፕሮግራም ይገኛል። ይህ ፕሮግራም ስልኩ በሚበራበት ጊዜ በራሱ የሚነሳ ሲሆን፣ ተጠቃሚው የሚያያቸውን ምስሎች፣ የጽሑፍ መልዕክቶች እና የሚጠቀምባቸውን መተግበሪያዎች በየጊዜው ፎቶ በማንሳት በስልኩ ሚስጥራዊ ፋይል ውስጥ ያስቀምጣል። ምንም እንኳን በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ “በየ 5 ደቂቃው ምስሎችን ቀጥታ ለፖሊስ ይልካል” የሚል ግነቶች ቢኖሩም፣ እውነታው ግን እነዚህ የተነሱ የስክሪን ምስሎች በስልኩ ማህደር ውስጥ ተቀምጠው የመንግሥት የደህንነት አካላት ወይም ፖሊሶች የዜጎችን ስልክ ድንገት በሚፈትሹበት ጊዜ ለክትትል መረጃነት የሚያገለግሉ መሆናቸውን ዓለም አቀፍ የዲጂታል መብት ተመራማሪዎች ያረጋግጣሉ። በተጨማሪም በሀገሪቱ ያሉ ስማርትፎኖች ከመንግሥት እውቅና ውጪ ያሉ የውጭ ሚዲያዎችን፣ የውጭ አገር ፊልሞችን ወይም መጻሕፍትን መክፈት እንዳይችሉ በዲጂታል ፊርማ የተቆለፉ ናቸው። የሰሜን ኮሪያ ባለሥልጣናት ይህንን ጥብቅ ቁጥጥር የሚያደርጉት የውጭ መረጃዎች እና ባህሎች ወደ ሀገሪቱ እንዳይገቡ ለመግታት በሚያደርጉት ሰፊ የሳንሱር ዘመቻ አካል እንደሆነ ይታወቃል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ