ነሐሴ 30 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) ድርጅቱ የልጆችን ማንነት አስጠብቆ ለመዝለቅ ከነሐሴ 28 እስከ መስከረም 3 ቀን 2019 ዓ.ም የሚቆይ የልጆችና የቤተሰብ ዓውደ ርዕይ አዘጋጅቷል። የቤተ እምነት ተቋማት የድርሻቸውን በሚገባ ባለመወጣታቸው የማንነት ቀውስ እየተስተዋለ መጥቷል ያሉት የሐመረ ብርሃን የብራና እና መጻሕፍት ሥራ ድርጅት ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ቃልኪዳን ብርሃኑ፣ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ድርጅታቸው ቀደም ሲል በጊዮን ሆቴል «ንጹሕ ምንጭ ኢትዮጵያ» በሚል ታላቅ ዓውደ ርዕይ ማካሄዱን አስታውተዋል። ዘንድሮም «ንጹሕ ምንጭ 2 – የምድር ጌጥ ኢትዮጵያ» በተሰኘ መሪ ቃል ዓውደ ርዕይ እያካሄዱ እንደሚገኙ ገልጸዋል። የቀደመውን ታሪክ ለልጆች በማሳወቅ ማንነቱን ጠብቆ የሚቀጥል ትውልድ ማፍራት እንደሚገባና ድርጅታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያቆየቻቸውን ታሪኮች ለልጆች በምስልና በድምፅ በማቅረብ የበኩሉን ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ አስረድተዋል። ሐመረ ብርሃን የብራና እና መጻሕፍት ሥራ ድርጅት በቀጣይም ህፃናት ላይ ትኩረት አድርጎ ታሪክን የማስተላለፍ ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ