ነሐሴ 29 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) በቻይና ዩናን ግዛት በሚገኘው የኒዙ ወንዝ ታላቅ ገደል ውስጥ የተገነባውና ፉያዎ ላደር በመባል የሚታወቀው የ288 ሜትር (945 ጫማ) ቁመት ያለው ክፍት የአየር ላይ ኤሌቬተር ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። ይህ ግዙፍ መዋቅር በገደሉ ግርጌ በሚገኘው ኒዙሄ በተባለች ገጠራማ መንደር የሚኖሩ ህፃናት በተራራው ጫፍ ላይ ወደሚገኘው አዳሪ ትምህርት ቤታቸው የሚያደርጉትን አስቸጋሪ መንገድ ለማቃለል ታስቦ የተገነባ ነው። እ.ኤ.አ. በ2022 የዩናን ግዛት ባለስልጣናት የዚሁ መንደር ህፃናት ለሰዓታት የሚወስደውን አደገኛ የተራራ ሽቅብ ጉዞ ሳይጠበቅባቸው ወደ ትምህርት ቤታቸው እንዲደርሱ በማሰብ 268 ሜትር ቁመት ያለው ቺንግዩን ላደር የተባለ ኤሌቬተር አስመርቀው ነበር። ተማሪዎቹ ወደ ጓንዛይ መንደር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመድረስ የሶስት ሰዓት ያህል አደገኛ ጉዞ ያደርጉ የነበረ ቢሆንም፣ በገደሉ ላይ የተገነባው ኤሌቬተር ግን በደቂቃዎች ውስጥ ተራራውን እንዲወጡ አስችሏቸዋል። ይህ ኤሌቬተር ሲመረቅ በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት ያገኘ ትልቅ የሎጂስቲክስ ስኬት የነበረ ቢሆንም፣ በሂደት ግን ለጉብኝት ወደ አካባቢው የሚጎርፉት ቱሪስቶች ቁጥር ከመጠን በላይ በመጨመሩ የተነሳ የኤሌቬተሩ አቅም አገልግሎቱን ለማሟላት አልቻለም። በመሆኑም ሰዎች ለሰዓታት ያህል በሰልፍ እንዲጠብቁ የሚያስገድድ ሁኔታ ተፈጠረ። ኤሌቬተሩ ለእነሱ ተብሎ የተሰራላቸው የአካባቢው ተማሪዎች አገልግሎቱን በነፃ የሚያገኙ ቢሆንም፣ በስራ በዛባቸው ቀናት ግን ረጅም ሰልፍን ለመጠበቅ ይገደዱ ነበር። በቅርቡ ከመጀመሪያው ኤሌቬተር ጎን ለጎን የተገነባው አዲሱ ፉያዎ ላደር ኤሌቬተር መመረቁን ተከተሎ ይህ የጥበቃ ጊዜ በግማሽ ቀንሷል። በዓለም ላይ ካሉ አስደናቂ ክፍት የአየር ላይ ኤሌቬተሮች አንዱ የሆነው አዲሱ ፉያዎ፣ ከመጀመሪያው ኤሌቬተር ይልቅ ፈጣን፣ ሰፊ እና የኤሌቬተር ማደሪያ ቱቦው በ20 ሜትር ረጅም ነው። ተማሪዎቹ አሁንም ቢሆን ወደ ኤሌቬተሩ ለመድረስ ማመላለሻ አውቶቡስ መጠቀም እና በመቀጠልም የአየር ገመድ ማጓጓዣ ኬብል ካር መሳፈር የሚጠበቅባቸው ቢሆንም፣ ከዚህ ቀደም ይወስድባቸው የነበረውን የሶስት ሰዓት ጉዞ እና የመልስ የስድስት ሰዓት መንገድ በማስቀረት በአሁኑ ወቅት በ30 ደቂቃ ውስጥ ትምህርት ቤታቸው መድረስ ችለዋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ