ነሐሴ 28 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) በሀገሪቱ የመጀመሪያው የሆነውን የቤት መግዣ ብድር መልሶ ማጠናከሪያ ኩባንያ ለማቋቋም የሚያስችል ታሪካዊ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ተፈራርመዋል። በአዲሱ ስምምነት መሠረት ተቋሙ በ100 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር ካፒታል የሚቋቋም ሲሆን፣ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የፋይናንስ አስተዋፅኦ ያደርጋል። ኩባንያው በባንክ ዘርፉ ውስጥ የሚስተዋለውን የጥሬ ገንዘብ ፍሰት አለመመጣጠን በመቅረፍ በመላው ሀገሪቱ ተደራሽ የሚሆን የቤት መግዣ ብድር ፋይናንስ ለማቅረብ ያለመ እንደሆነ ተገልዟል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ስለ ስምምነቱ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ይህ አጋርነት ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸውና የዜጎችን ክብር የጠበቁ 1.5 ሚሊዮን ቤቶችን ለማቅረብ የታቀደውን ግብ ለማሳካት ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ጠቁመዋል። አክለውም እርምጃው በፋይናንስ ሥርዓቱ ውስጥ የግል ዘርፉን ተሳትፎ ለማስፋት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ገልፀው፣ ኢትዮጵያ ፈጣን፣ ጠንካራ እና ሁሉንም ያካተተ ኢኮኖሚ የመገንባት ጉዞዋን አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል። ይህ የሁለቱ ተቋማት ስምምነት በሀገሪቱ የቤት ልማት ፋይናንስ አቅርቦት ላይ የታየውን ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት በመቅረፍ ረገድ አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል ተብሎ ይጠበቃል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ