ግንቦት 20 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የዓለምን የኃይል ሚዛን ሊቀይር ይችላል የተባለውና በከፍተኛ ሚስጥር ሲገነባ የቆየው የቻይናው አዲሱ የጦር መርከብ (Type 004 Aircraft Carrier) ግንባታ እጅግ በሚያስደንቅ ፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን የሚያሳዩ አዳዲስ የሳተላይት መረጃዎች ይፋ ሆነዋል።
የዓለም አቀፍ የስትራቴጂክ ጥናት ማዕከል (CSIS) በቅርቡ ይፋ ባደረገው የሳተላይት ምስል ትንተና መሠረት፣ በቻይናው ዳሊያን የባህር ወደብ (Dalian Shipyard) ላይ እየተገነባ ያለው የዚህ ግዙፍ የጦር መርከብ አካል (Hull) በአሁኑ ወቅት 286 ሜትር ርዝመትና 46 ሜትር ስፋት ላይ መድረሱ ተረጋግጧል። ይህ አስገራሚ መጠን መርከቡ ለንግድ አገልግሎት የሚውል ሳይሆን፣ እስካሁን በቻይና ባህር ኃይል ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ እጅግ ዘመናዊና ግዙፍ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ መሆኑን ማረጋገጫ ሆኗል።
በዚህ መርከብ ግንባታ ላይ ዓለም አቀፍ የጦር ባለሙያዎችን ይበልጥ ያስገረመውና ትኩረት የሳበው ጉዳይ መርከቡ የሚጠቀምበት የኃይል ምንጭ ነው። በሳተላይት ምስሎቹ ላይ የታዩት የውስጥ መዋቅሮች መርከቡ በኒውክሌር ኃይል (Nuclear Propulsion) የሚንቀሳቀስ መሆኑን በግልጽ ያሳያሉ። ይህ ከሆነ መርከቡ ከ110 ሺህ እስከ 120 ሺህ ቶን የሚመዝን ግዙፍ አቅም የሚኖረው ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የዓለምን ውቅያኖሶች በበላይነት እየተቆጣጠረች ከምትገኘው የአሜሪካው ጄራልድ አር ፎርድ (Gerald R. Ford-class) የኒውክሌር ጦር መርከብ ጋር እኩል አሊያም የሚበልጥ አቅም እንዲኖረው ያደርገዋል።
የዚህ ግዙፍ መርከብ ግንባታ በዚህ ሳምንት ይህን ያህል ፍጥነት ሊያሳይ የቻለው ቻይና በባህር ኃይል ግንባታ ዘርፍ በምታስተዋውቀው አዲስ የሞዱላር ቴክኖሎጂ (Modular Technology) ምክንያት ነው። መርከቡ በአንድ ቦታ ላይ ከመገንባት ይልቅ፣ የተለያዩ ትላልቅ ክፍሎቹ በተለያዩ ፋብሪካዎች በተናጠል ተዘጋጅተው በቀጥታ ወደ ማደሪያው (Dry dock) በመምጣት እንደ ዕቃ መገጣጠሚያ በአጭር ጊዜ ውስጥ እየተገጣጠሙ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ምንም እንኳን መርከቡ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ ባህር ላይ ሙከራ ለመግባት የተወሰኑ ዓመታት የሚቀሩት ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት በዳሊያን የታየው ባለ 286 ሜትር የጦር መርከብ አካል ቻይና በዓለም አቀፍ ውቅያኖሶች ላይ ያላትን የባህር ኃይል የበላይነት ለማረጋገጥና አሜሪካን ለመገዳደር በከፍተኛ ፍጥነት እየተጓዘች መሆኑን የሚያሳይ ማረጋገጫ ሆኗል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ