ነሐሴ 25 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የካሳ ክፍያ በክልሎች እንዲፈጸም የሚደነግገው አዲሱ አዋጅ እስካሁን ማስፈጸሚያ መመሪያና ደንብ እንዳልወጣለት ለመናኸሪያ ሬዲዮ የተናገሩት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት አመራርና አሰራር ክትትል ስራ አስፈጻሚ አቶ ድጉማ ነዳ ናቸው። አዋጁ የካሳ ክፍያና የካሳ ግምቶች በሙሉ በክልል ደረጃ እንዲፈጸሙ የሚደነግግ መሆኑ በበጎ የሚጠቀስ ቢሆንም፣ በአፈጻጸም ደረጃ ግን አስቸጋሪ እንደሆነ ተናግረዋል። ክልሎች ካሳ ለመክፈል በቂ በጀት የሌላቸው ሆኖ መገኘቱ አዋጁ ተፈጻሚ እንዳይሆን ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ዋነኛው እንደሆነም ጠቅሰዋል። ይህም እውነታ አዋጁ ከወጣ በኋላ ወደ ስራ በገቡ ፕሮጀክቶች ላይ ከፍተኛ ተግዳሮት መፍጠሩን አቶ ድጉማ ገልጸዋል። በፌደራል ደረጃ ጣልቃ እንዳይገባ አዋጁ ይከለክላል፤ በክልሎች እንዳይፈጸም ደግሞ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ጉዳዩ ዳግም ውይይት የሚፈልግ መሆኑን አስረድተዋል። በካሳ ክፍያ አፈጻጸም ችግር ምክንያት በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም ባንክና በሌሎችም ዓለም አቀፍ አጋሮች ድጋፍ የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች መጓተታቸውን ተናግረዋል። ችግሩን ለመፍታት መንግስት በድጋሚ ጥናት እያስጠና መሆኑን የገለጹት አቶ ድጉማ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጉዳዩን በደብዳቤ ማሳወቁንም አክለዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ ነባር እና አዳዲስ ክሶች እንዳሉበት የጠቆሙት አቶ ድጉማ፤ በአሁኑ ወቅት በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሚታዩ፣ እንዲሁም እስከ ህገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ድረስ የደረሱ በርካታ ክሶች እንዳሉ ተናግረዋል። አሁን ላይ ማስፈጸሚያ መመሪያ እና ደንብ ወጥቶ ወደ ስራ መግባት እንደሚያስፈልግ የገለጹት አቶ ድጉማ፣ ክልሎች ለሜጋ ፕሮጀክቶች ካሳ የመክፈል አቅም እንዲኖራቸው በበጀት ቀመራቸው ስለሚሰሩ ፕሮጀክቶች መጠንና አይነት አስቀድመው እንዲያውቁ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። ይህም ስራ የገንዘብ ሚኒስቴርን እና የአዋጁ አስፈጻሚ የበላይ አካል የሆነውን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴርን ክትትል እንደሚፈልግ አብራርተዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከካሳ ክፍያ ጋር በተገናኘ የ7 ቢሊየን ብር ክስ እንዳለበት በቅርቡ ማስታወቁ ይታወሳል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ