ነሐሴ 26 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) በአገራችን እየተከናወኑ ባሉ የሥራ ዕድል ፈጠራና የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥራዎች ውስጥ የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት እና ተስማሚ የመሥሪያና መሸጫ ቦታ አለመኖር ዘርፉን ሲፈትኑ የቆዩ ዋና ዋና ማነቆዎች መሆናቸውን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታውቋል። ያጋጠመውን የብድር አቅርቦትና የመሥሪያ ቦታ ችግር ለመፍታት በርካታ የተቀናጁ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ያሉት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ፣ በተለይም በኦሮሚያ ክልል የከተማ አስተዳደሮች እና ወረዳዎች የመሥሪያና መሸጫ ቦታዎችን በመገንባት፣ ለባንኮች የራሳቸውን ዋስትና (ኮላተራል) በማስያዝ ወጣቶች በብድር አቅርቦት ታቅፈው የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ማስቻላቸውን ተናግረዋል። አዳዲስ አሠራሮች ሥራ ላይ መዋላቸውን የጠቀሱት አቶ ሰለሞን፣ በዲጂታል ፋይናንስ አማካኝነት እንደ ቴሌብር ባሉ አሠራሮችና በባንኮች በኩል የአነስተኛ ብድር አገልግሎት መስፋፋቱን ገልጸዋል። ተበዳሪዎች ብድር የሚመልሱበትን ሁኔታ መሠረት በማድረግ ከ5 ሺሕ እስከ 10 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ብድር በማቅረብ፣ ለሚሊዮን ኢንተርፕራይዞችና ግለሰቦች የፋይናንስ አቅርቦት ማቻሉን ጠቁመዋል። የመሥሪያና የመሸጫ ቦታ ችግርን በመንግሥት ሼዶች ብቻ መፍታት ባለመቻሉ፣ በጓሮ መሬት ላይ በሚገነቡ የቤተሰብ ቢዝነሶች ከ280 ሺሕ በላይ ኢንተርፕራይዞች እንዲፈጠሩና ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር አዳዲስ የመሥሪያ ቦታዎች እንዲመቻቹ መደረጉን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ